Friday, March 13, 2015

እንግሊዝ ከሰብአዊ መብቶች ጋር በተያያዘ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን እርዳታ ማቋረጡዋን አስታወቀች

መጋቢት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ብሉምበርግ የእንግሊዝ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው እንግሊዝ በኢትዮጵያ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ለመደጎም ትሰጥ የነበረውን እርዳታ ያቋረጠችው፣ መንግስት መጪውን ምርጫ ተከትሎ ጋዜጠኞችንና የተቃዋሚ ፓርቲ አባሎችን ማሰሩንና መዋካቡን በመቀጠሉ ነው።
የእንግሊዝ አለማቀፍ የልማት ተራድኦ ጸሃፊ ጀስቲን ግሪኒንግ ፣ እንግሊዝ አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑዋን ተከትሎ፣ ቀድም ብሎ ይሰጥ የነበረው የማህበራዊ አግልግሎት ድጋፍ እንደተቋረጠ ለእንግሊዝ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው አስረድተዋል።

ባለስልጣኑ በኢትዮጵያ የሚፈጸመው የሰብአዊ ና የፖለቲካ ነጻነቶች ገፈፋ አሳሳቢ መሆኑ እርዳታው እንዲቋረጥ አድርጎታል። በተለይም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ ነጻ ምርጫ የማካሄድና የጸጥታ ሃይሎችን ተጠያቂ የማድረጉ ነገር አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ለተወሰደው እርምጃ ምክንያት መሆኑን ባለስልጣኑ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
የእንግሊዝ ተራድኦ ድርጅት በዚህ አመት 368 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም በኢትዮጵያ ብር 11 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለመስጠት አቅዳ ነበር፧ ባለፉት አምስት አመታት ከ700 ሚሊዮን ፓውንድ ያላነሰ ገንዘብ ደግፋለች።
ዘገባው እንደሚለው አስቀድሞ የተመደበው ገንዘብ የህዝብ መረታዊ አግልግሎቶችን ከመደጎም ይልቅ ሌሎች የጤና፣ የትምህርትና የውሃ ስራዎችን ለማገዝ ይውላል። እንዲህ አይነቱ ድጋፍ የእንግሊዝ መንግስትን ከተጠያቂነት የሚያድነው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግስትም የተለየ ሃላፊነት እንዲወጣ አያስገድደውም ብሎአል።
በሌላ ዜና ደግሞ በደቡብ ኦሞ የሚካሄደው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ በአካባቢው የጸጥታ መደፍረስ ሊያስከትል ይችላል በሚል ለጋሽ አገራት ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ከቻይና የልማት ባንክ በተገኘ ብድር 6 የስኳር ፋብሪካዎችን ለመገንባትና 150 ሺ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የሸንኮራ ገዳ ተክል ለማካሄድ ማቀዱን የሚገልጹት ለጋሽ አገራት፣ ፕሮጀክቱ በአካባቢው በባህላዊ መንገድ በከብት እርባታ ኑሮአቸውን የሚገፉትን ማህበረሰቦች ህይወት ከማወኩም በላይ ለግጭት መንስኤ ሊሆን ይችላል።
በመቶሺዎች የሚቆጠሩ የፋብሪካ ሰራተኞች ወደ አካባቢው በሚጓዙበት ወቅት ፣ የብሄር ግጭቶችን ሊያባብስ ይችላል በሚል ለጋሾቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
27 አገራት በጋራ በመሆን ባወጡት መግለጫ እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው እሩጫ፣ በተለይም የቦዲና የሙርሲ ማህበረሰቦችን ህይወት የሚያውክ በመሆኑ፤ በአካባቢው ብጥብጥና አለመረጋጋት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች የኦሞ ወንዝ ፍሰት በሚገነባው የግልገል ግቤ 3 የሃይል ማመንጫ ግድብ አማካኝነት የሚቀንስ ከሆነ የግጦሽና ለም የሆኑ ቦታዎችን እንደሚያጡ ስጋታቸውን ገልጸዋል። መንግስት ስለሚገነቡት የስኳር ፋብሪካዎች ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ፣ የአካባቢውን ህዝብ ፍላጎት በጽሞና እንዲያዳምጥ፣ ግጭትን ለማስወገድ ሲባል ለግንባታው የሚያደርገውን እሩጫ እንዲገታ 27ቱ ለጋሽ አገራት ጠይቀዋል።


No comments:

Post a Comment