Tuesday, June 10, 2014

ወያኔ ያሰራቸው አራቱ ሀኪሞች

     ቪኦኤ እንደዘገበው  በቅርቡ በስራ አፈጻጸም ተግባሩ ተሸላሚ ከሆነው ከነቀምቴ ሆስፒታል አራት ሃኪሞች ታስረው በነቀምቴው የምሥራቅ ወለጋ ማረሚያ ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የታሰሩት ሐኪሞችም ዶ/ር አዳም ለማ- የቀዶ  ጥገና ሐኪም፣ ዶ/ር ኢሣያስ ብርሃኑና ዶ/ር በላይ ቤተማርያም -የማኅፀንና የፅንስ ስፔሻሊስቶች፣ ዶ/ር ታመነ አበራ- የቀድሞ የሆስፒታሉ የሕክምና ዳይሬክተርና አሁን ለስፔሻላይዜሽን የጥቁር አንበሣ ፕሬዚደንት ሐኪም ሲሆኑ፤የተሰናበቱት ኮሪያዊ ሐኪም ደግሞ  የአጥንት ስፔሺያሊስት የሆኑት ዶ/ር ሪም ጆንግ ሆ ናቸው።
እንደ ቪ ኦ ኤ ሪፖርት ሁሉም ሐኪሞች በነቀምቴ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ አገልግለዋል፡፡ ኮርያዊው ሐኪም ከሥራ ሲሠናበቱ፤ አራቱ ኢትዮጵያዊያን ግን በቁጥጥር ሥር ውለው ነቀምቴ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡
​የእነዚህ ለረዥም ዓመታት አገልግሎት ሰጥተዋል የሚባሉ ሐኪሞች ከሥራቸውና ከደመወዛቸው መታገድ፣ አልፎም መታሠር መነጋገሪያ እየሆነ ነው፡፡
ሐኪሞቹ ስለታሰሩበት ምክንያት የተጠየቁት የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮምሽን ቃል አቀባይ ኮማንደር አበበ ለገሰ  ሐኪሞቹ ከሙያዊ ሰነ ምግባር ውጪ  ትክክል ያልሆነ ህክምና እና ቀዶ ጥገና በመስጠት ለሶስት  ሴቶች ሞት ምክንያት እንደሆኑ በሟች ቤተሰቦች የተመሰረተውን ክስ ተከትሎ በጥርጣሬ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
በቅርቡ የነቀምት ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት ዾክተር ጫላ አኦላኔ በበኩላቸው መንግስት የእናቶች ሞት የመቀነስ እቅድ አቅዶ ሳለ በኛ ሆስፒታል ግን  ባለፉት ስድስት ወራት ከወሊድ ጋር በተያያሰ 16 እናቶች መሞታቸው ከእቅዱ በተቃራኒ እየሄደ መሆኑን ያሳያል ብለዋል። በመሆኑም ችግሩ በሐኪሞች ቸልተኝነት እና በቂ የህክምና ክትትል ካለመስጠት  የመጣ መሆኑን እና አለመሆኑን ማጣራት ስለሚያስፈልግ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተናግረዋል።
የሐኪሞቹ ቤተሰቦች ግን ውንጀላውን አይቀበሉትም።በስራቸው ጣልቃ በመግባት ሐኪሞቹን ማዋከብ የተጀመረው ቀደም ብሎ መሆኑን የተናገሩት ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንዲት የዶክተር አዳም ለማ ቤተሰብ ተናግረዋል።
ሞተዋል ከተባሉት ሶስት ሴቶች መካከል አንዷን ቀዶ ጥገና ያደረጉላቸው ዶክተር አዳም መሆናቸውን እንደምሳሌ ያወሱት የቤተሰብ አባሉዋ፤ ታማሚዋ ያረፉት በተደረገው የእንቅርት ቀዶ ጥገና ሳይሆን ህመሙ ከባድ እና በደማቸውና ወደ ሌላ አካላቸው የተሰራጬ ስለነበር ነው ብለዋል።
የሙዋች አስክሬን ወደ ምኒልክ ሆስፒታል ለምርመራ ተወስዶ ሟች የሞቱት በህክምና አሰጣጥ ችግር ሳይሆን በሳንባ ካንሰር መሆኑ ተረጋግጡዋል ያሉት የቤተሰብ አባሉዋ፤ ሐኪሙ ምንም ችግር እንደሌለባቸው በሪፖርት የተገለጸ ቢሆንም ፖሊሶች “መታሰር አለባቸው”በማለት ክ25 ዓመታት በላይ በከተማዋ ያገለገሉትን እና በማህበረሱ ዘንድ ከፍ ያለ ተቀባይነት ያላቸውን ሐኪሞች እንዳሰሩዋቸው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment