Wednesday, June 11, 2014

የግንቦት 7 አራተኛ ጉባኤ አቋም መግለጫ


የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አራተኛ ጉባኤ ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓም ተጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ከተካሄደና ህዝባዊ ትግሉን ወደፊት የሚያራምዱ ውሳኔዎችን ካሳለፈ በኋላ ባለፈዉ ሰኞ ምሽት እጅግ በጣም በደመቀ ሁኔታ ተጠናቀቀ። ይህ የንቅናቄው አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ንቅናቄው ባለፉት ሁለት አመታት የተጓዘባቸውን መንገዶች፤ ያቀዳቸውን ስራዎችና የዕቅዱን አፈጻጸም በጥልቀትና በስፋት በመዳሰስ መጪው የትግል ወቅት የሚጠይቀውን የመስዋዕትነት ደረጃ ከወዲሁ ተመልክቶ ዘረኛዉን የወያኔ አገዛዝ በማስወገድ የኢትዮጵያን ህዝብ የፍትህና የዲሞክራሲ ጥማት ሊያረኩ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን አበይት ውሳኔዎች አሳልፏል።

የግንቦት 7 አራተኛ መደበኛ ጉባኤ የንቅናቄዉን የአለፉት አምስት አመታት ጉዞና በዚህ በአራተኛው ጉባኤ ላይ የሃላፊነት ዘመናቸውን የጨረሱትን የንቅናቄው ምክር ቤትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የስራ ዕቅድና የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል። በሪፖርቱ ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይት ካካሄደ በኋላ፣ ጉባኤው ለመረጣቸው አዲስ የአመራር አባላት ንቅናቄው ያሰበውን ግብ እንዳይመታ አንቀው የያዙትን እንቅፋቶች ሊወገዱ የሚችሉበትን ሁኔታዎች ተነጋግሮ መግባቢያ ላይ ደርሷል።

ከዚህም በተጨማሪ ንቅናቄው ጥንካሬ ባሳየባቸው መስኮች አቅሙን አጠናክሮ በይበልጥ በመስራት የኢትዮጵያ ህዝብ ከንቅናቄው የሚጠብቀውን የታሪክ አደራ እንዲወጣ አሳስቧል።  በጉባኤው ወቅት አባላት ያደረጉት አመራሩን የመንቀፍ፤ አቅጣጫ የማሳየት፤ ሀሳብ የማመንጨትና በአጠቃላይ በጉባኤው በቀረቡ ጉዳዮች ላይ ያሳዩት ንቁ ተሳትፎ ንቅናቄው በህዝባዊ አመጽና እምቢተኝነት ዘርፎች ብቻ ሳይሆን በዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍም እያደገ መምጣቱን በግልጽ አሳይቷዋል።

የግንቦት 7 አራተኛ መደበኛ ጉባኤ ከምክር ቤትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የስራ ሪፖርት በተጨማሪ፤ የኦዲትና የስራ ቁጥጥር፣ እንዲሁም የስነ ስርአትና የግልግል ኮሚቴ ሪፖርቶችን አዳምጦ ሰፊና ጥልቅ ውይይት ካካሄደ በኋላ በሪፖርቶቹ ላይ አስፈላጊውን ትችት አካሂዳ አጽድቋቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የንቅናቄውን ስትራቴጂና ይህንኑ ስትራቴጂ ተሸክሞ በተግባር የሚተረጉመውን መዋቅር በአጽንኦት ከፈተሸ በኋላ በስትራቴጂው ላይ መጠነኛ ለውጥ በማድረግ የስትራቴጂውንና የመዋቅር ለውጡን ተቀብሎ አጽድቋል። ይህ የንቅናቄው አራተኛ ጉባኤ ንቅናቄውን ላለፉት ሁለት አመታት የመሩትንና ያገለገሉትን የምክር ቤት፤ የስራ አስፈጻሚ፣ የኦዲትና የስራ ቁጥጥር፣ የስነ ስርአትና ግልግል ኮሚቴ አባላት ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግኖ በማሰናበት፣ በምትካቸዉ ንቅናቄውን ለሚቀጥሉት ሁለት አመታት የሚያገለግሉ ሊቀመንበርና ዋና ጸሃፊ፣ የምክር ቤት አባላት፤ የኦዲትና የስራ ቁጥጥር፤ እንዲሁም የስነ ስርአትና ግልግል ኮሚቴ አባላትን መርጧል።

አራተኛዉ የግንቦት 7 መደበኛ ጉባኤ ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበትን አጠቃላይ ሁኔታ በዝርዝር ከመረመረ በኋላ፣ ዘረኛዉን የወያኔ አገዛዝ ለማስወገድ የሚደረገው ትግል፣ በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገሮችም ስለሆነ፣ የንቅናቄው አባላት ወያኔ ባለበት ሁሉ ለማስወገድ የሚደረገውን ትግል አጠናክረው ከቀጠሉ፣ የወያኔ ስርአት ያለምንም ጥርጥር የሚሸነፍ መሆኑን በማሳሰብ፣ ወያኔን በማስወገድ ተግባር ላይ በያሉበት እንዲያተኩሩ አሳስቧል።

ከተለያዩ አገሮች የመጡ የግንቦት 7 አባላትን ያሰባሰበዉ አራተኛዉ የግንቦት 7 መደበኛ ጉባኤ የትግል ቃል ኪዳን የታደሰበት፤ የመስዋዕትነት ዝግጅት የታየበትና አባላት የትግልና የስራ ልምድ የተለዋወጡበት፣ ከምን ግዜዉም በላይ የተሳካና የተዋጣለት ጉባኤ ነበር። በመጨረሻ፣ የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አራተኛ ጉባኤ ለአባላቱና በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ አዲስ የትግል ጥሪ በማስተላለፍ ደማቅ በሆነ ስነሰርአት ተፍጽሟል።



የግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣


No comments:

Post a Comment