Saturday, June 21, 2014

ፍትህ ያጡ የምዕራብ ወለጋ ተፈናቃዮች

የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ከምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢና ከቄለም ወለጋ ዞን የተፈናቀሉ አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ያቀረበውን ዘገባ ተከትሎ ኢሳት ከጊምቢ በታች በሚገኘው አሹ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑትን እንዲሁም ተፈናቅለው ባህርዳር ከሚገኙት መካከል አንዳንዶቹን አነጋግሮ እንደተረዳው ፍትህ አጥተው የሚሰቃዩ ወገኖች በብዙ መቶዎች ይቆጠራል።
አሹ ቀበሌ ውስጥ የሚኖረው በንግድ ስራ የሚተዳደረው ወጣት እንደተናገረው ወንድሙ አካባቢውን ለቆ ባህርዳር ቢገባም፣ እርሱና ቤተሰቡ ግን ለመውጣት አልቻሉም። ” መውጣት መግባት አልቻንልም፣ ንብረት ተቃጥሎአል፣ ሰዎችም ተገድለዋል” የሚለው ወጣቱ፣ የአካባቢው ባለስልጣናት እጅ አለበት ብሎ እንደሚያምን ገልጿል። ድርጊቱን የሚፈጽሙትን ወጣቶች የሚያደራጁት ልዩ ሃይሎች፣ ፖሊሶችና ባለስልጣኖች መሆናቸውን ከድርጊታቸው መረዳት ይችላል ብሎአል
ተፈናቅለው ባህርዳር ከሚገኙት መካከል  ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው ኢትዮጵያዊ ደግሞ ፖሊሶች ልበሳቸውን ቀይረው እየመጡ ድርጊቱን የሚፈጽሙትን እንደሚያበረታቱዋቸው ገልጿል
የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተፈናቃዮችን ቢያነጋገሩዋቸውም፣ ምንም አይነት መፍትሄ ሊሰጡዋቸው አለመቻላቸውን ተፈናቃዮች ተናግረዋል ጉዳዩን በማስመልከት ጥያቄ ያቀረብንላቸው የመኢአድ የሰሜን ቀጠና ሃለፊ ኢንጂነር ሽፈራው ዋሌ የክልሉ መንግስት ሰዎቹን በአድማ በታኝ ፖሊስ ከመስተዳድሩ አካባቢ እንዲርቁ ማድረጉን ገልጸዋል
ተፈናቅለው ወደ ባህርዳር ከመጡት መካከል አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውንም ኢ/ር ሽፈራው ገልጸዋል
በጉዳዩ ዙሪያ የአማራ ክልል እና የኦሮምያ ክልል ባለስልጣኖችን ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። ይሁን እንጅ የኦሮምያ  የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ራብያ ኢሳ ተፈናቃዮቹ መቶ የማይሞሉ መሆናቸውን ገልጸው ፣ አንድ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ እና 2 የሌሎች ብሄር ተወላጆች መሞታቸውን ገልጸው መንግስት ሌሎችም እንዳይፈናቀሉ፣ የተፈናቀሉትም እንደሚለሱ የአማራ ክልልና የኦሮምያ ክልሎች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል

No comments:

Post a Comment