Friday, June 13, 2014

በጎደሬ ወረዳ አካባቢ በምትገኘው ጻኑ  ግጭት ተቀሰቀሰ


በጎደሬ ወረዳ አካባቢ በምትገኘው ጻኑ ሃሙስ  ሰኔ 5 ፣ 2006 ዓም  የተነሳው ግጭት ለበርካታ ዜጎች መፈናቀል ምክንያት መሆኑን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የወረዳው ባለስልጣናት ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የሌሎች አካባቢ ተወላጆችን አካካቢውን ለቀው እንዲወጡ ማዘዛቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ በረካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በአሁኑ ጊዜ ቴፒ ከተማ ውስጥ ሰፍረው እንደሚገኙ ታውቋል። በግጭቱ ምን ያክል ሰዎች እንደተጎዱ ባይታወቅም አንድ ፖሊስ መገደሉን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።
የፌደራል እና የክልል ፖሊሶች በአካባቢው የፓትሮል ቅኝት እያደረጉ ሲሆን፣ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ ተቋርጧል።
ግጭቱ የተነሳው የወረዳው ባለስልጣናት ጻኑ የሚባለው በደቡብ ክልል ስር የሚገኘው አካባቢ የጋምቤላ መሬት ነው የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውንና ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ሰዎችን በማስወጣት የአካባቢውን ተወላጆች ለማስፈር በመፈለጋቸው ነው። የጋምቤላ ክልል ሰፋፊ መሬቶች ለውጭ ባለሀብቶች እና ለህወሃት የቀድሞ ታጋዮችና በስልጣን ላይ ላሉ የመከላከያ ሰራዊት አዛዦች በስፋት መሰጠቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
እስካሁን ድረስ ምን ያክል ሰዎች እንደተፈናቀሉ በቁጥር ለማወቅ የተደረገው ጥረት አልተሳካም። አካባቢው በቡና ምርቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በርካታ የደቡብ፣ የአማራና የሌሎች ብሄረሰቦች ተወላጆች ይኖሩበታል።

No comments:

Post a Comment