Friday, August 18, 2017

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉና በቀበሌ ቤት የሚገኙ የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች ከአቅማቸው በላይ ከፍተኛ የኪራይ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተወሰነባቸው።

(ኢሳት ዜና ነሐሴ 12/2009) በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉና በቀበሌ ቤት የሚገኙ የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች ከአቅማቸው በላይ ከፍተኛ የኪራይ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተወሰነባቸው። ለ30 እና 40 ዓመታት 5 ብር በወር ይከፍሉ የነበሩ በአዲሱ ተመን ከ200 እስከ 300 ብር እንዲከፍሉ እየተጠየቁ መሆናቸውን ከወሊሶ ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል። ነዋሪው በወር በደመወዝ የማያገኘውን ብር ለቀበሌ ቤት እንዲከፍል በመወሰኑ ቁጣውን እየገለጸ መሆኑም ታውቋል። በወሊሶ ባለፈው ሳምንት የተጀመረው አድማ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችልም እየተነገረ ነው። ከመዲናዋ አዲስ አበባ በ114ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ከ100ዓመት በላይ እድሜን ያስቆጠረች፡ የቀደምትነቷን ያህል በስልጣኔው ብዙም ያልገፋች ከተማ ናት- ወሊሶ። ከአዲስ አበባ – ወደ ጂማ የሚወስደው መንገድ መሃል ለመሃል ሰንጥቆ የሚያልፍባት ወሊሶ በንግድ እንቅስቃሴ ሞቅ ያለች እንደሆነች ይነገርላታል።
የህዝብ ብዛቷ በ2007 እንደ አሮፓውያን አቆጥጠር በተደረገ ቆጠራ 38ሺህ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አስተዳደራዊ መዋቅር መቀመጫ በመሆን የምታገለግለው ወሊሶ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዋሪዋ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮውን የሚገፋ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የተለያዩ የጥናት ወረቀቶች ያመለክታሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በህዝብ ተቃውሞ በተደጋጋሚ ስሟ የሚነሳው ወሊሶ በመላው ኦሮሚያ በተካሄደው ህዝባዊ አመጽ በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ከተሞችም አንዷ ናት። በቅርቡም ከግብር ጭማሪ ጋር በተያያዘ ለተከታታይ ቀናት የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ቆይታለች። የወሊሶ ነዋሪ አብዛኛው በቀበሌ ቤት የሚኖር ነው። ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውም በአረቄ፡ በጠላና በሌሎች አነስተኛ የንግድ ስራዎች የሚተዳደር ከዕለት ጉርስ ያለፈ ገቢ የሌለው እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። በቀድሞ መንግስታት የተገነቡና በተለይ በደርግ ዘመን ወደ መንግስት ባለቤትነት የተዛወሩ ቤቶች ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል በአነስተኛ ኪራይ እንዲኖርባቸው የተደረጉ ሲሆን አብዛኞቹ ቤቶች በእርጅና ምክንያት የፈራረሱ፡ ናቸው። ከ2ብር ጀምሮ እስከ 10 ብር የሚከራዩት እነዚህ ያረጁና የፈራረሱ ቤቶች ከ40ዓመታት በኋላ ዋጋቸው እንዲጨምር መደረጉ ነው ሰሞኑን በወሊሶ ቁጣን ያስነሳው። የወሊሶ ከተማ አስተዳደር ባለፉት 20 ዓመታት በዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚገኙ የቀበሌ ቤቶችን በማፍረስ ለባለሀብቶች ሲሰጥ መቆየቱን የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች፡ ከተማዋን በማህበራዊ ትስስር ያቀኑ ቀደምት ነዋሪዎች ተፈናቅለው ከከተማዋ ውጪ እንዲኖሩ መገደዳቸውን ያነሳሉ። ሰሞኑን የወሊሶ ከተማ አስተዳደር ከዋናዋና መንገዶች ውጪ ያሉትንና በቀበሌ ይዞታ ስር የሚገኙ ቤቶችን በሙሉ ለማፍረስና ቦታውን ለባለሀብቶች ለመስጠት በሚል በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉትን የከተማዋ ነዋሪዎችን የመኖር ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ውሳኔ ማስተላለፉ ተሰምቷል። የቤት ኪራዩን መጠን ከ20እጥፍ በላይ በመጨመር ከአቅም በላይ ገንዘብ በመጠየቅ ተከራዩ ተገፍቶ አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ መወሰኑ ለአብዛኛው ነዋሪ አስደንጋጭ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በከተማዋ አስተዳደር ውሳኔ መሰረት በወር 5 ብር ይከፍሉ የነበሩ የቀበሌ ቤት ነዋሪዎች ከ200 እስከ 300 ብር እንዲከፍሉ ይገደዳሉ። በአዲሱ የኪራይ ውሳኔ መሰረት የቀበሌ ቤት ዝቅተኛው 50 ብር ከፍተኛው ደግሞ 400 ብር የክፍያ ተመን ወጥቶለታል። ይህም ማለት በአንድ የቀበሌ ቤት ላይ ከ20 እስከ 100 እጥፍ የደረሰ ጭማሪ የተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። በኑሮ ውድነት ለሚሰቃየውና በልቶ ማደር ብርቅ እየሆነበት ለመጣው አብዛኛው የወሊሶ ከተማ ነዋሪ ውሳኔው የመርዶ ያህል እንዳስደነገጠው ከአከባቢው ያነጋገርናት ወጣ ገልጻልናለች። የቤት ኪራዩ በዚህን ያህል መጠን ከፍ እንዲል የተደረገው ነዋሪው መክፈል አቅቶት አከባቢውን ለቆ እንዲሄድና መሬቱን ለባለሀብቶች ለመስጠት ታቅዶ እንደሆነ ይነገራል። ትከሻው በኑሮ ውደነት የጎበጠበት የወሊሶ ነዋሪ የተቆለለበት ኪራይን ሊከፍል የሚችል እንዳልሆነ እየታወቀ ውሳኔው መተላለፉ ሆን ተብሎ ለማፈናቀል የተወሰደ እርምጃ ነው ተብሏል። ነዋሪው የከተማዋን አስተዳደር ውሳኔ በመቃወም ሰልፍ ሊያደርግ እየተዘጋጀ እንደሆነ ይነገራል። በህዝባዊ ተቃውሞና አድማ ለሰነበተችው ወሊሶ የነዋሪውን ብሶት የሚጨምር እርምጃ በመወሰዱ በውጥረት ላይ እንድትሆን እንዳደረጋት ተገልጿል። በሚቀጥለው ሳምንት በተጠራው አጠቃላይ የኦሮሚያ ተቃውሞ ወሊሶ ከወዲሁ እየተዘጋጀች ሲሆን የከተማዋ አስተዳደር ውሳኔ ተቃውሞውን ያባብሰውዋል ተብሎ ይጠበቃል


No comments:

Post a Comment