Tuesday, August 8, 2017

በኢትዮጵያ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋው ተረጅዎች ቁጥር ወደ 8.5 ሚሊዮን አሻቀበ

ኢሳት ዜና ( ነሃሴ 2 ቀን 2009 ዓም) በኢትዮጵያ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋው ተረጅዎች ቁጥር ወደ 8.5 ሚሊዮን አሻቀበ
ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ድርቅ ምክንያት እለታዊ አፋጣኝ የምግብ ረድኤት ያስፈልጋቸው ከነበሩ 7.8 ሚሊዮን ተረጅዎች ወደ 8.5 ሚሊዮን ከፍ ማለቱን የብሔራዊ አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ከተመድ እና ሌሎች ዓለምአቀፍ የረድኤት ድርጅቶች የጋራ ጥናት አስታውቋል። እንደ ግብረሰናይ ድርጅቶቹ ጥናት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኢሊኖ የዓየር መዛባትን ተከትሎ የርሃብ ተጠቂዎች ቁጥር ከዚህ በላይም ሊጨምር እንደሚችል የጥናት ቡድኑ ስጋቱን አመላክቷል።

የእለት ከእለት የምግብ እርዳታ ጠባቂ የሆኑ ዜጎችን ሕይወት አስቀድሞ ለመታደግ እና ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይደርስ የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አፋጣኝ እርዳታ እንዲያደርግ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ቀውስ ቡድን ጠይቋል። በምግብ ሴፍቲኔት ለታቀፉ 4 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ችግረኞች ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያስፈልጋል። እስካሁን የአሜሪካ መንግስት 137 ሚሊዮን ዶላር ልገሳ ያደረገ ሲሆን ከጉዳተኞች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ልገሳው በቂ አይደለም።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 8.5 ሚሊዮን ረድኤት ጠባቂዎች ያሉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ በቂ የሆነ ተመጣጣኝ ምግብ ማግኘት የተሳናቸው 3.6 ሚሊዮን ታዳጊ ሕጻናቶች እና ነፍሰጡር እናቶች መሆናቸውንም የጥናት ሪፖርቱ አሳውቋል። የንጹሕ መጠጥ ውሃ እና የምግብ እርዳታ ጠባቂዎች ቁጥር ወደ 10.5 ሚሊዮን ማሻቀቡን እና የቤት እንስሳትን ለመታደግ በ2.2 ሚንዮን ዶላር ወጪ የመጠለያ ጣቢያዎች ተሰርተዋል። በተለይ የአርብቶአደር አካባቢዎች በድርቁ ምክንያት በቀዳሚነት የረሃቡ ገፈት ቀማሽ ቀጠናዎች ተብለው ተመድበዋል።
በተመሳሳይም በትግራይ 24 ወረዳዎች ውስጥ ከ436 ሰዎች በላይ ውሃ በቀላቀለ ተቅማጥ በሽታ ተጠቅተዋል። ለተቅማጥ በሽታው መስፋፋት የንጹህ ውሃ አቅርቦት አለመኖር በምክንያትነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ በተለይ ከበሽተኞቹ አብዛኛውን ቁጥር የሸፈነው የመቀሌ ከተማ ሲሆን እስካሁን 255 ታማሚዎች ተመዝግበዋል። የከተማው ነዋሪዎች ንጹህ ውሃ ማግኘት ባለመቻላቸው የወንዝ እና የኩሬ ውሃ ለመጠቀም ተገደዋል። የትግራይ ጤና ቢሮው ውሃ ወለዱን በሽታ ለመከላከል ክፉኛ ተጎጂ በሆኑ ወረዳዎች 20 አባላት ያለው የደጋ መከላከል ቡድን ማቋቋሙን ሪሊፍ ዌብ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment