Tuesday, August 8, 2017

በወልድያ አምቦ እና በሌሎችም ከተሞች የነጋዴዎች አድማ ለ2ኛ ቀን ሲቀጥል በባህርዳር ደግሞ ሱቆች ታሸጉ

ኢሳት ዜና ( ነሃሴ 2 ቀን 2009 ዓም)
ነጋዴዎች በዘፈቀደ የሚጣለውን የቀን ገቢ ግምትን ታሳቢ ያደረገውን ግብር በመቃወም የሚያደርጉት የስራ ማቆም አድማ እየተካሄደ ነው። በደብረታቦር፣ ወልድያ፣ አምቦ ፣ ጉዳርና ጎንጪ እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም ሰናን ወረዳ የንግድ ድርጅቶች ተዘግተው አድማዎች እየተካሄደ ነው። በአምቦ ለሚቀጥሉት 3 ቀናት የቆያል በተባለው አድማ፣ ከግብር ጥያቄ በተጨማሪ በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞችም እንዲፈቱ ይጠይቃሉ። የአምቦ ህዝብ በአንድ ሃሳብ ሆኖ ተቃውሞውን በጽናት እያካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። አገዛዙ በከተማው ህዝብ ላይ የሚያደርሰው ከፍተኛ ጫና የአምቦን ህዝብ መንፈስ መስበር አለመቻሉንም እነዚህ ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

አምና በግፍ የተገደሉትን የነጻነት ሰማዕታት ለመዘከር የባህርዳር ከተማ ህዝብም እንደ አምቦ ህዝብ በአንድ ሃሳብ በመሆን የንግድ ድርጅቶችን በመዝጋት ለአንድ ቀን ያሳየው ተቃውሞው፣ መቀመጫውን በዚሁ ከተማ ላደረገው ብአዴን ትልቅ ሽንፈት ሆኖ በመቆጠሩ ፣ የብአዴን መሪዎች በንግድ ድርጅቶች ላይ የተለያዩ የቅጣት ውሳኔዎችን ለማሳለፍ እየመከሩ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ የንግድ ድርጅቶች የታሸጉ ሲሆን፣ ድርጅቶቹ ስለሚጣልባቸው ቅጣት በቅርቡ ይገለጻል ተብሎ ይጠበቃል። ወኪላችን ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች፣ ድርጅቶቻቸውን ዘግተው የነጻነት ጀግኖቻቸውን በመዘከራቸው የህሊና እርካታ ማግኘታቸውን፣ ልጆቻቸውን ያጡ ቤተሰቦችም መደሰታቸውን ተናግረዋል። አገዛዙ የሚጥልባቸው የቅጣት ውሳኔ ይበልጥ እንዲታገሉ እንጅ እንዲያፈገፍጉ እንደማያደርጋቸው ነጋዴዎች ይገልጻሉ። በተለያዩ የግለሰቦች ቤቶች ሻማዎች እየበሩ ሰማዕታቱ ሲዘከሩ እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጻለች።
በወልድያ ከተማ ለሁለተኛ ቀን የሚካሄደውን አድማ አስመልክቶ ወኪላችን ያጠናከረው ዘገባ እንደሚያመለክተው ደግሞ ፣ የከተማው ባለስልጣናት ነጋዴዎች የንግድ ድርጅቶቻቸውን እንዲከፍቱ ለማድረግ የተለያዩ የማስፈራሪያ ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ነው። 55 ሺህ ብር አመታዊ ግብር የተጣለባቸው የወልዲያው ነጋዴ ዛሬ ሱቃቸውን አልከፈቱም። ጨርቃ ጨርቅ የሚነግዱት ከድር ኡስማን (ስማቸው የተቀየረ) ለከተማው የግብር መሥሪያ ቤት አቤት ቢሉም መፍትሔ አላገኙም። የተጣለባቸው ግብር "የተሳሳተ ነው" ብለው አቤቱታ ሲያቀርቡ "ትከፍላላችሁ ትከፍላላችሁ " የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ድርጅታቸውን በመዝጋት ወደ ተቃውሞ መግባታቸውን ይናገራሉ።
የነጋዴዎች ተቃውሞውን ካስተባበሩት መካከል በሕንጻ መሳሪያዎች ንግድ የተሰማሩት ግለሰብ ፣ "ጣሪያ የነካ የግብር ክፍያ እንድንከፍል ነው የተገደድነው።" ይላሉ። በሁለት ሱቆቻቸው 13,000 ብር የቀን ገቢ ያገኛሉ ተብሎ ግምት የተጣለባቸው ነጋዴው፣ ለቅሬታ ሰሚ የመንግሥት አካላት አቤት ቢሉም ምላሽ ባለማግኘታቸው ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር ተማክረው ሱቃቸውን ዘግተዋል። የመንግሥትን ግብር ተቃውመው ሱቆቻቸውን የዘጉት ግን የጨርቃ ጨርቅ እና የሕንፃ እቃዎች ነጋዴዎቹ ብቻ አይደሉም።
በወልዲያ ከተማ ጎንደር በር፣ አዳጎ እና ፒያሳ በተባሉ አካባቢዎች የንግድ ሱቆች ተዘግተው ውለዋል። ፖሊሶች ድርጅቶችን በግዳጅ ለማስከፈት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። ነጋዴዎቹ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤም ደርሷቸዋል።
ግብር በመላው አገሪቱ ነጋዴዎችን እያስለቀሰ ነው። በመራዊ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች በቅርቡ ከዞኑ አመራሮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ከመጠን በላይ የሚጣልባቸው ግብር እጅግ እንዳስመረራቸው ይናገራሉ። ዘንድሮ “ግብር መጣል ሳይሆን ሰው መጣል ነው” የተያዘው የሚሉት ነዋሪዎች፣ ህዝቡ በግብር የተነሳ እያበደ ነው ይላሉ። ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን እየመለሱ መሆኑንም ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment