Thursday, August 3, 2017

አርዱፍ የትጥቅ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ

የአፋር አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር -አርዱፍ፣የአፋር ብሎም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነቱን እስኪቀዳጅ ድረስ የህወኃት አገዛዝን ለማስወገድ የጀመረውን የትጥቅ ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ድርጅቱ በላከው መግለጫ በአሁኑ ወቅት የሙስና ዘመቻ የሚል ድራማ የጀመረው የህወኃት አገዛዝ በሌላ በኩል የብሄር ብሄረስቦችን ቀንን በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ ለማክበር በሚል በርሀብ፣ በድህነትና በችግር ላይ የሚገኘውን የአፋር ሕዝብ ለበዓሉ የሚሆን ገንዘብ አዋጣ በማለት እንሥሶቹን እንዲሸጥ እያስገደደው እንደሆነ አመልክቷል።
በአፋር ክልል ጨርሶ መልካም አስተዳደርና ማህበራዊ ፍትህ የሚባል ነገር እንደማይታወቅ የጠቀሰው አርዱፍ፣ክልሉ እየተመራና እየተዳደረ ያለው መቀመጫውን አዲስ አበባ ባደረገው በፌዴራል መንግስቱ ሳይሆን መቀሌ በሚገኘው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ነው ብሏል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 በአዲስ አበባ ከተካሄደው የአፋር ብሄራዊ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ኮንግረስ በኋላ፣ ህወኃት የክልሉን ሥልጣን በስዩም አወል ለሚመራው ቡድን ለመስጠት እንደወሰነ ያወሳው አርዱፍ፣ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአፋር ክልል የሚተዳደረው በትግራይ ክልል መሆኑን ጠቁሟል።
ወዲያውኑ በስድስተኛው የኤ ኤን ዲ ፒ ጉባኤ ያለ አፋር ህዝብ ውክልና እና ይሁንታ ስዩም አወል የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆኖ መሾሙን መግለጫው አውስቷል።
ስዩም ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጡን ተከትሎ በዙሪያው ዘመዶቹን በማሰባሰብ በህወኃት የተሰጠውን ተልዕኮ እየፈጸመ እንደሚገኝ የጠቀሰው መግለጫው፣ የቀድሞው ኢስማኤል አሊ ሴሮም ሆነ ስዩም አወል የአፋርን ህዝብ ከማገልገል ይልቅ ለህወኃት አለቆቻቸው እየሰገዱ መኖርን የመረጡ መሆናቸውን አትቷል።
እንደ አርዱፍ መግለጫ በአፋር ክልል ለሚካሄዱ ነገሮች በሙሉ አዋጅ፣መመሪያና ውሳኔ የሚተላለፈው በትግራይ ክልል ምክር ቤት ሲሆን፤ የአፋር ክልል ምክር ቤት ምንም ዓይነት ውሳኔ በራሱ ለማሳለፍም ሆነ ለመሥራት ሥልጣን የለውም።
“የአፋር ሕዝብ ያለ ነጻነት በፍርሃት እየኖረ ነው፤የአፋር ክልል በረሃብና በጠኔ እየተሰቃዬ ነው” ያለው አርዱፍ፤ የህወኃትን አጀንዳ ለማስፈጸም ፍቃደኛ ያልሆኑ አፋሮች ከአርዱፍ ጋር ግንኙነት አላችሁ እየተባሉ ከህግ አግባብ ውጪ እንደሚታሰሩ፣እንደሚደበደቡና እንደሚወገዱ አመልክቷል።
በስዩም አወል አመራር ጎሰኝነት የክልሉን ፖለቲካ ተቆጣጥሮታል የሚለው አርዱፍ፤ የአፋር ሕዝብ ሌላው ቀርቶ እንዴት መናገርና ማሰብ እንዳለበት እየተወሰነለት ነው ብሏል።
በኢትዮጵያ የአድሎ አገዛዝ ተወግዶ የተሻለ ፍትሀዊ ስርዓት ለማምጣት የሚታገሉ ተቃዋሚዎች የህዝብን ፍላጎን ባማከለ መልኩ ትግላቸውን እንዲያደርጉ የመከረው መግለጫው፤” እኛ አርዱፎች የራሳችንን ድርሻ ለማድረግ ከመቼውም በላይ ዝግጁ ነን” ብሏል።
አርዱፍ አክሎም ሆነ ብሎ የአፋርንና አጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ እያሸበረና እያተራመሰ ያለውን የህወኃት አገዛዝ ለማስወገድና በምትኩ የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎቱን በራሱ የሚወስንበትና ዋስተኛ የሚሆነው እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈን የጀመረውን የትጥቅ ትግል አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።


No comments:

Post a Comment