Monday, May 29, 2017

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን በመስራችነትና በዋና ስራ አስፈጻሚነት ያገለገሉት ዶ/ር ጌታቸው በትሩ በገዛ ፈቃዳቸው ስራ ለቀቁ

ኢሳት (ግንቦት 21: 2009)
በቅርቡ የብድር መጠኑ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሶ የነበረውን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንን በመስራችነትና በዋና ስራ አስፈጻሚነት ለ10 አመታት ያገለገሉት ዶ/ር ጌታቸው በትሩ በገዛ ፈቃዳቸው ስራ መልቀቃቸው ታውቋል።
ሃላፊው ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ቢረጋገጥም ምክንያቱ ግን በኮርፖሬሽኑም ሆነ በዶ/ር ጌታቸው አልተገለጸም። መንግስታዊ ተቋም በሃገሪቱ ሰፊ የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ ለማካሄድ ባቀደ ጊዜ ዶ/ር ጌታቸው ፕሮጄክቶችን በመቆጣጠርና በማስተባበር ይሰሩ እንደነበር ታውቋል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ስራውን በአዲስ መልክ ከጀመረ ከ 10 አመት በፊት ጀምሮ ፕሮጄክቶችን ለማካሄድ ከተለያዩ አካላት የወሰደው የብድር መጠን ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ደረሶ እንደነበር ኮርፖሬሽኑ ለፓርላማ ይፋ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ፕሮጄክት ግንባታ ከተለያዩ ባለሙያዎች ዘንድ ሳይቀር በዲዛይን ስራ ላይ ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።
የዶክተር ጌታቸው በትሩ ከስራ መልቀቅ ተከትሎ በምትካቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር እንደሆኑ የተነገራላቸው ዶ/ር ብርሃኑ በሻህ ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር መሾማቸውን ለመረዳት ተችሏል።
ዶ/ር ጌታቸው ከሃላፊነታቸው መቀቃቸውን በተመለክተ አስተያየት እንዲሰጡ ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ መቅረቱን ጋዜጣው በዘገባው አመልክቷል።

No comments:

Post a Comment