Friday, May 26, 2017

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የአንድ አመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት በየነ

ኢሳት (ግንቦት 18 ፥ 2009)
የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሰሞኑን የጥፋተኝነት ብይን በተላለፈበት ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው ላይ የአንድ አመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣር አርብ ሰጠ።
ጋዜጠኛው የተላለፈበት የ 18 ወር እስራት ከእስር ቆይታው ጋር የሚቀረረብ በመሆኑ ተከሳሹ አመክሮ ታስቦለት ከእስር  ይወጣል የሚል ግምት መኖሩን የህግ አካላት ገልጸዋል። ይሁንና ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እስከ አርብ ከሰዓት በኋላ ድረስ ከእስር አለመለቀቁን ለመረዳት ተችሏል። ከሳሽ አቃቤ ህግ ተከሻሹ ህገመንግስቱን ለመናድ የሚያስችሉ የአመፅ እንቅስቃሴዎች እንዲባባሱ አስተዋጽዖ አድርጓል ሲል ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
ጋዜጠኛ ጌታቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ላይ በጋዜጠኛ አበበ ገላው ለቀረበባቸው ተቃውሞ ድጋፍ ሰጥቷል የሚል ክስ ቀርቦበታል።

ይሁንና የጋዜጠኛው ጠበቃ ደንበኛቸው በማህበራዊ ድረገፅ አድርጎታል የተባለውን ግንኙነት እንዳልፈጸመ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ምላሽ ሰጥተዋል። ጋዜጠኛ ጌታቸው ከመነሻው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ቢመሰረትበት አቃቤ ህግ ክሱን በማሻሻል አመፅን ማነሳሳት በሚል መደበኛ ወንጀል ክስ መቀየሩ ይታወሳል።
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤቱም ከቀናት በፊት በሰጠው የመጀመሪያ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብትና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶች ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ኮንነዋል።
ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈው ብይንም በሃገሪቱ ሃሳብን በነጻነት ለመግለፅ በሚደረግ ጥረት ላይ አፈናን ለማሳደር የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን እነዚሁ አካላት ገልጸዋል። የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛው በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ለእስር መዳረጉ የሚታወስ ነው።
ባለፉት አምስት ወራት ተመሳሳይ ብይን የተላለፈባቸው ጋዜጠኞች ቁጥር ሶስት የደረሰ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ለእስር ተዳርገው የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር 15 መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
በመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ውስጥ ይሰራ የነበረው ጌታቸው ሽፈራው በኦሮሚያ ክልል ሲካሄድ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲሁም ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሲዘግብ ቆይቷል።
የፌደራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሃሙስ ባስተላለፈው ተመሳሳይ ፍርድ በቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ላይ የስድስት አመት ከሶስት ወር የእስር ቅጣት ማስተላለፉ ይታወሳል።
ዮናታን ተስፋዬ በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ ባሰፈራቸው አስተያየቶቹ ለእስር መዳረጉና የተላለፉበት የእስር ቅጣት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚያመለክት ነው ሲል የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment