Wednesday, May 10, 2017

ለምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በድጋሚ ጭማሪ ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመድ ገለጸ

ኢሳት (ግንቦት 2 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር በድጋሚ ጭማሪን ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ።
በቅርቡ መንግስትና ድርጅቱ ባወጡት የተረጂዎች ቁጥር መረጃ 5.6 ሚሊዮን አካባቢ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ተረጂዎች በ2.2 ሚሊዮን በማደግ 7.8 ሚሊዮን መድረሱ ይፋ ተደርጓል።
የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለእርዳታ ጥሪ እየሰጠ ያለው ምላሽ አነስተኛ መሆንና በድርቁ በተጎዱ አካባቢዎች በበልግ ወቅት መጣል የነበረበት ዝናብ በበቂ ሁኔታ ባለመጣሉ ምክንያት የድርቁ አደጋ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል።
በዚሁ ተደራራቢ ችግር ሳቢያ የተረጂዎች ቁጥር በቅርቡ ጭማሪን እንደሚያሳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድርቁን አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርቱ አመልክቷል። 
ይሁንና የተረጂዎች ቁጥር በምን ያህል ሊጨምር እንደሚችል ድርጅቱ የሰጠው ትንበያ የሌለ ሲሆን፣ በተለይ በሶማሌ ክልል የምግብ እጥረቱና የኮሌራ በሽታ ወረርሽን እያደረሰ ያለው ሰብዓዊ ጉዳት እየከፋ መምጣቱ ተገልጿል። መንግስት በበኩሉ 7.8 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች የምግብ እጥረት አስከትሎ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመታደግ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ርብርብ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርቧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና መንግስት ባወጡት የእርዳታ ጥሪ ለተረጂዎች ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ይሁንና ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊገኝ የቻለው የገንዘብ ድጋፍ 200 ሚሊዮን ዶላር እንኳን ያልደረሰ ሲሆን፣ የእርዳታ ተቋማት ድርቁን ለመከላከል አፋጣኝ ርብርብ ካልተደረገ የሰብዓዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል ብቻ 6ሺ 619 ህጻናት ወደ ማገገሚያ ማዕከል ገብተው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ሲሆን፣ በምግብ እጥረት ሳቢያ ጉዳት የሚደርስባቸው ህጻናት ቁጥር በደቡብ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በመጨመር ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም በሶማሌ ክልል ዕልባት ሊያገኝ ያልቻለው የውሃ እጥረት የኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው ዘመቻ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ታውቋል። ድርቁ ጉዳት እያደረሰባቸው ካሉ ከ70 ወረዳዎች መካከል የኮሌራ ወረርሽኙ በ40 ወረዳዎች ውስጥ በመዛመት ላይ መሆኑ ተመልክቷል።
የክልሉ የጤና ቢሮ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በወረርሽኙ ምክንያት በሰው ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ቢያረጋግጡም በበሽታው የሞቱ ሰዎችን ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ወደ 1ሺ 200 አካባቢ የጤና ባለሙያዎች ተሰማርተው የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆኑም ችግሩ ዕልባት አለማግኘቱን ለመረዳት ተችሏል።
በቅርቡ በተለያዩ የክልሉ ስፍራዎች የተከሰተው የኩፍኝ ወረርሽኝ በሽታ ተጨማሪ የጤና ስጋት መሆኑን ድርጅቱ አክሎ አስታውቋል።

No comments:

Post a Comment