Monday, May 29, 2017

በህይወት መኖራቸው ያልታወቁት የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ልዑል ገብረማሪያም ከስራቸው እንዲሰናበቱ ተወሰነ

ኢሳት (ግንቦት 21: 2009)
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህይወት ይኑሩ አይኑሩ ያልታወቀ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ልዑል ገብረማሪያም ከስራቸው እንዲሰናበቱ ወሰነ።
ለበርካታ አመታት በፍትህ ስርዓት ውስጥ ያገለገሉት አቶ ልዑል ላለፉት ስምንት ወራት ውስጥ በስራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ ሲሆን፣ ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ የመስሪያ ቤታቸው ባልደርቦች ዳኛው ያሉበትን ሁኔታ እንደማያውቁ ለፓርላማው የቀረበን ሪፖርት ዋቢ በማድረግ ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት አቶ ልዑል ገብረማሪያም በህመም ምክንያት በስራ ገበታቸው መገኘት አልቻሉም ቢባልም ጉዳዩን ማረጋገጥ እንዳልቻለ አመልክቷል።

“ዳኛው በህይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚታወቅ ነገር የለም” ያለው አስተዳደሩ ባለቤታቸውም ምንም መረጃ እንደሌላቸው ለፓርላማ ባቀረበው ማብራሪያ ገልጸዋል።
የቀረበለትን ሪፖርት ያደመጠው ምክር ቤቱም የገቡበት ያልታውቀው ዳኛው ከስራቸው እንዲሰናበቱ ወስኗል።
አቶ ልዑል ዕድሚያቸው 57 አመት የሞላ በመሆኑ የጡረታ መብታቸው ተከብሮ ከግንቦት 1 ቀን 2009 አም ጀምሮ እንዲሰናበቱ ሲል አክሎ አስታውቋል።
ዳኛው በህይወት ይኑሩ አይኑሩ የሚለው ጉዳይ መወያያ ሆኖ ቢቀርብም ምላሽ ሳይገኝለት መቅረቱ ታውቋል።
ከ1990 አም ጀምሮ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በዳኝነት ሲያገለግሉ የነበሩት ዳኛው የ1997 አም ምርጫን ቀውስ ተከትሎ ክስ በተመሰረተባቸው የቀድሞ የቅንጅት አንድነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ጉዳይ እንዲሁም በድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የነፍስ ማጥፋት ክስ ካስቻሉ ዳኞች መካከል አንዱ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።
የዳኛው መሰናበት ተከትሎም በቅርቡ በምትካቸው አዲስ ዳኛ ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።

No comments:

Post a Comment