Wednesday, May 31, 2017

የመን ወደ መፈራረስ እያመራች መሆኑን ተመድ ገለጸ



ኢሳት (ግንቦት 23 ፥ 2009)
በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው የመን ሙሉ ለሙሉ ወደ መፈራረስ እያመራች መሆኗን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።
ሃገሪቱ ያጋጠማት የረሃብ አደጋና ዕልባት ማግኘት ያልቻለው የዕርስ በርስ ጦርነት የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና የመንግስታዊ ተቋማት መፈራረስ አደጋ እንዲጋረጥባቸው ማድረጉን የድርጅቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ሃላፊዎች ይፋ ማድረጋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የየመን ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ሪፖርተን ያቀረቡት የማስተባሪያ ቢሮው ሃላፊ ስቴፋን ኦብሪየን በየመን ቀጥሎ ባለው የዕርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ከ 17 ሚሊዮን የሚበልጡ የሃገሪቱ ሰዎች ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጣቸውን አስታውቀዋል።
ለከፋ የምግብ እጥረት ተጋልጠው ከሚገኙት መካከል ወደ 7 ሚሊዮን የሚሆኑት ለረሃብ አንድ ደረጃ በቀረው አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ሃላፊው ገልጸዋል።

የአለም አቀፍ ማህበር ወደ መፈራረስ እያመራች ያለችውን ሃገር በአስቸኳይ እንዲታደግ ጥሪያቸውን ያቀረቡ ኦ’ብሪያን ባለፉት ሁለት ወራት ከ55 ሺ የሚበልጡ የመናውያን በኮሌራ በሽታ ወረርሽኝ ለህመም መዳረጋቸውን ለጸጥታው ምክር ቤት አስረድተዋል።
500 የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ በሽታ ወረርሽኝ መሞታቸውን የጠቆሙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተወካዮች በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ውስጥ በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 150 ሺ አካባቢ ሊደርስ እንደሚችል አክለው ገልጸዋል።
ሃገሪቱ አሁን ላለችበት ሁኔታ ታጣቂ ቡድኖች እያካሄዱ ያለው ግጭት ዋነኛ ምክንያት ቢሆንም፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ለችግሩ ዕልባት ለመስጠት መዘግየቱን ሃላፊው በሪፖርታቸው አመልክተዋል። መንግስት ላጋጠመው የሰብዓዊ ቀውስ 2.1 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ ቢገልጽም እስካሁን ድረስ ሊገኝ የቻለው ከሩብ በታች መሆኑም ታውቋል።
በሃገሪቱ ከሁለት አመት በፊት በተለያዩ አንጃዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ከስምንት ሺ በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ወደ 45ሺ አካባቢ የሚሆኑ የመናውያን ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ከመረጃዎቹ ለመረዳት ተችሏል።
በቀድሞ የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ደጋፊ ታጣቂዎችና በሁቲ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለውን ግጭት ዕልባት ለመስጠት የተለያዩ ጥረቶች ቢካሄዱም፣ ድርድሩ ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል። ሳውዲ አረቢያ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ ካላቸው ከቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዚደንት አብድ ራቡ ማንሱር ጎን በመቆም ወታደራዊ ዘመቻን እያካሄደች ሲሆን፣ ኢራን ለሁቲ አማጺያን ጎን መቆሟ ይነገራል።
እነዚሁ የሁቲ አማጺያን ለፕሬዚደንቱ ከሃገር መኮብለል ምክንያት የሆኑ ሲሆን፣ መዲናዋ ሰንዓ ከተማን ጨምሮ አብዛውን የየመን ሰሜናዊ ክፍል ተቆጣጥረው ይገኛሉ።
በመንግስት ስራ ላይ የነበሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰራተኞች ደሞዝ ሳይከፈላቸው ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውም ተመልክቷል።

No comments:

Post a Comment