Tuesday, February 14, 2017

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ በምዕራብ እና አርሲ ዞን ብቻ ከ240 ሰዎች በላይ መገደላቸው ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 7 ፥ 2009)

የአስቸኳይ ጊዜ መታወጁን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና አርሲ ዞን ብቻ በ20 ቀናት ውስጥ 240 ሰዎች መገደላቸውን የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ ገለጸ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ከመስከረም 28/2009  እስከ ጥቅምት 18/2009 በአርሲ ነገሌ ብቻ 70 ሰዎች ሲገደሉ፣ 335 መታሰራቸውን የገለጸው የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ፣ ከዚህ በተጨማሪም በሻላ እና አጄ በተባሉ አካባቢዎች 85 ሰዎች ሲገደሉ 400 የሚሆኑት ደግሞ መታሰራቸውን ገልጿል።
የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በላከው በዚሁ ባለ ዘጠኝ ገፅ ሪፖርት በኦሮሞዎች በይበልጥም በወጣቶች ላይ የተነጣጠረው ጥቃት እኤአ ከ2005 ጀምሮ ላለፉት ለ12 አመታት ተጠናክሮ መቀጠሉን ዘርዝሯል።

በተለይም የመብት ጥያቄዎችን ለአንድ አመት ያለማቋረጥ መጠየቃቸውን ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ረገጣው መባባሱን፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደግሞ ግድያው መጠናከሩን ዘርዝረዋል።
በሁለቱ ትልልቅ ክልሎች በብዛት ሁለቱ ብሄሮች በሚኖሩባቸው ኦሮሚያና አማራ ክልሎች ጠንካራና የተቀናጀ ህዝባዊ እንቅስቃሴ መከሰቱን ተከትሎ፣ ሃገሪቱ በጠንካራ ወታደራዊ ቁጥጥር ስር መውደቋን የገለጸው የሊጉ መግለጫ፣ የዶ/ር መረራ ጉዲናን የአቶ በቀለ ገርባንና የሌሎችንም የፖለቲካ መሪዎች እስራት አስታውሷል።
በኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ አንድ ሺህ ሰዎች ተገድለው 40 ሺህ ያህሉ ወደ እስር ቤት መጋዛቸውን በ9 ገፅ ሪፖርቱ የጠቆመው የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ፣ ከመስከረም 28/2009 እስከ ጥቅምት 18/2009 በአርሲ ዞንና በምዕራብ ኦሮሚያ ዞን ብቻ የተገደሉ 240 ሰዎችን በየወረዳው በዝርዝር አስቀምጧል። በተጠቀሱ ቦታዎች ብቻ የታሰሩ 3ሺህ 760 መሆናቸውም ተመልክቷል።
በ20 ቀናት ውስጥ 248 ሰዎች ከተገደሉባቸው 14 ወረዳዎች በሻላ እና አጄ 85 ሰዎች ሲገደሉ 400 የሚሆኑ ታስረዋል። በአርሲ ነገሌ 70 ሰዎች ሲገደሉ፣ በዶዶላ 17, በቆሬ 25 ሰዎች ተገድለዋል። በአጠቃላይ በ14ቱ ወረዳዎች በ20ቀናት 3ሺህ 706 ሲታሰሩ 248 መገደላቸውን ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ሊግ ያቀረበው የሊጉ ሪፖርት ያስረዳል።

No comments:

Post a Comment