Friday, March 3, 2017

በኦሮሚያና ሶማሌ ድንበር አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እየተዛመተ መሆኑ ተገለጸ

ኢሳት (የካቲት 24 ፥ 2009)
የኦሮሚያ ክልልን ከሶማሌ ክልል ጋር በሚያዋስኑ የድንበር አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ያለው ግጭት ዕልባት አለማግኘቱንና ወደ ተለያዩ ቀበሌዎች በመዛመት ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ።
በምስራቅ ሃረርጌ ጨናቅሳን ተብሎ በሚጠራ ከተማ ያሉ ነዋሪዎች የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች የኦሮሚያ ክልልን ጥሰው በመግባት እየፈጸሙት ባለው ጥቃት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከ100 በላይ ነዋሪዎች መገደላቸውን አስታውቀዋል።
በዚሁ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብዱራህማን ዱባ ታጣቂዎች ከጨንቃሳን በተጨማሪ በባቢሌ፣ በጉርሱም እና በተለያዩ መንደሮች መዛመቱን ለአዲስ ስታንዳርድ መጽሄት አስረድተዋል።
ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ የሶማሌ ክልል ታጣቂዎች በኦሮሚያ ክልል እየፈጸሙት ባለው ጥቃት ከሁለቱም ወገኖች ከ400 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል

በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ከአንድ ሳምንት በፊት ቦርደዴ ተብሎ በሚጠራ ወረዳ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት በትንሹ 30 ሰዎች መገደላቸውን አቶ አብዱራህማን አክለው ገልጸዋል።
ተመሳሳይ ጥቃቶች በባሌ ዞን በስወና በመዳ ወላቡ እና ባዳዌ ስራር ወረዳዎች የተፈጸሙ ሲሆን፣ በጉጂ ዞን ስር በሚገኙ የተለያዩ ቀበሌዎች ድንበርን ዘልቀው የገቡ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች ጉዳት ማደረሳቸውንም አመልክቷል።
በአካባቢው ያለው ግጭት ዕልባት ባለማግኘቱ ሳቢያ የደረሰውን የሰውና የንብረት ጉዳት በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች እየወሰዱ ያለውን ዕርምጃ ድንበር የማስፋፋት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ለማግኘት ያለመ እቅድ እንዳለው ሲገለፅ ቆይቷል።
በፌዴራል መንግስት ድጋፍ ይደረግላቸዋል የተባሉት እነዚሁ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይሎች በነዋሪዎች ላይ እየወሰዱ ካለው ጥቃት በተጨማሪ በርካታ ንብረቶችን እንደዘረፉም የኦፌኮ አመራሮች ይገልጻሉ።
በአካባቢው ተሰማርቶ የሚገኘው ኮማንድ ፖስት ለችግሩ ዕልባት ከመስጠት ይልቅ የችግሩ አካል መሆኑን ነዋሪዎች ለመጽሄቱ በሰጡት ቃለምልልስ አክለው አስረድተዋል።
የፌዴራል መንግስት በአካባቢው ባለው ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ቢያረጋግጥም የሞቱ ሰዎች ቁጥር ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ትላንት ሃሙስ የኦሮሚያ ፓርላማ በክልሉ ፕሬዚደንት አቶ ለማ መገርሳ ሰብሳቢነት በቴሌቪዥን ይቀርብ በነበረ ፕሮግራም በርካታ የፓርላማ አባል በሶማሌ ልዩ ፖሊስ እንዲሁም በፌዴራል ፖሊስ በድንበር አካባቢ እየተፈጸመ ነው ባሉት ግድያና ሃብት የተሰማቸውን ቅሬታ ሲገልፁ መቆየታቸውን አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት በጉዳዩ ዙሪያ ሪፖርት አስፍሯል።
በአካባቢው ያለው ግጭት እየተስፋፋ መምጣቱን ተክትሎ ባለፈው ሳምንት በጨናቅሳን ከተማ የሚኖሩ ነዋሪዎች ልዩ ፖሊስ ወደ ከተማዋ እንዳይገባ ለማድረግ መንገድ ዘግተው እንደነበርም ለመረዳት ተችሏል።


No comments:

Post a Comment