Tuesday, February 14, 2017

የግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት በኬንያውያን ላይ ተፅዕኖ ማሳደር መጀመሩን ሂውማን ራይትስ ዎች ገለጸ

ኢሳት (የካቲት 7 ፥ 2009)

በቅርቡ ግንባታው የተጠናቀቀው የግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት በኬንያ የቱርካና ሃይልና በኢትዮጵያ በታችኛው የስምጥ ሸለቆ በሚኖሩ በግማሽ ሚሊዮን ነዋሪዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳደር መጀመሩን ሂውማን ራይትስ ዎች ማክሰኞ አስታወቀ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የቱርክና ሃይቅ የውሃ ከፍታ መጠን ካለፈው የፈረንጆች አመት ጀምሮ በ1.5 ሜትር ቀንሶ መገኘቱን የአሜሪካ የዕርሻ መምሪያ መረጃን ዋቢ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መገለጫ አመልክቷል።
የሃይል ማመንጫው ስራ መጀመር እና በተጓዳኝ እየተካሄደ ያለ የመስኖ ስራ የወንዙ ውሃ መጠን እንዲቀንስ በማድረግ በዙሪያው በሚኖሩ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖን ሊያሳድር እንደሚችል ሂውማን ራይትስ ዎች ስጋቱን ገልጿል።

በቱርካና ሃይቅ ላይ አሳን በማስገርና የእርሻ ስራዎችን በማካሄደ ህይወታቸውን የሚመሩ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ የሁለቱ ሃገራት ዜጎች የወንዙ መጠን በመቀነሱ ምክንያት የዕለት ከእለት ኑሯቸው ክፉኛ ጉዳት እየደረሰበት እንደሚገኝ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው ተግባራዊ ያደረገው የልማት ስራ በስፍራው ያሉ ነዋሪዎችን ህልውና አደጋ ውስጥ መክተት አይገባውም ሲሉ በሂውማን ራይትስ ዎች የሰብዓዊ መብቶች ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን አስታቀዋል።
ለግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ውሃ መያዣ የተገነባው ውሃ ማጠራቀሚያ ወደ ቱርካና ሃይል የሚፈሰውን ውሃ መጠን እንዲቀንስ በማድረጉ የወንዙ ውሃ መቀነስ እያሳየ መምጣቱን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ቃለመጠየቅ ያደረገላቸውን ነዋሪ ዋቢ አድርጎ ባስደገፈው በዚሁ ሪፖርት በርካታ በሃይቁ ዙሪያ የሚኖሩ የኢትዮጵያና የኬንያ ተወላጆች በአካባቢው ከፍተኛ የውሃ መጠን መቀነስ መታየቱን ተናግረዋል።
በሃይቁ ላይ እየደረሰ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ እና የአካባቢውን ጥበቃ ዋስትና ለማስጠበቅ የኢትዮጵያና የኬንያ መንግስታት አፋጣኝ መፍትሄ ማፈላለግ እንዳለባቸው ሂውማን ራይትስ ዎች አሳስቧል።
የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቱን ተግባራዊ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት በአካባቢው የሚደርሰውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የወሰደው ዕርምጃ አለመኖሩን የድርጅቱ የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ ፊሊክስ ሆንር አክለው ገልጸዋል።
ከሁለት ወር በፊት ሃይል ማመንጨት የጀመረው የግልገል ጊቤ ሶስተኛ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ጎን ለጎን የመስኖ ልማት ስራ የሚካሄድበት በመሆኑ የሚደርሰው ተፅዕኖ እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችል ተሰግቷል።
በፕሮጄክቱ ዙሪያ 19ሺ 500 ሄክታር መሬት ለሸንኮራ አገዳ ተክል መከለሉን የገለጸው ድርጅቱ ተጨማሪ 10ሺ 500 ሄክታር መሬት ለመስኖ ልማት ተከልሎ እንደሚገኝ በሪፖርቱ አስፍሯል።
ለፕሮጄክቱ በአጠቃላይ 100ሺ ሄክታር መሬት ለሸንኮራ አገዳ ዕርሻ ሊከለል እቅድ መኖሩም ታውቋል።
ከኢትዮጵያ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቱ በአካባቢው ባሉ ነዋሪዎች ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም ሲል ማስተባበያ ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

No comments:

Post a Comment