Monday, February 6, 2017

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በ6 አየር ሃይል አባላት ላይ የእስራት ቅጣት አስተላለፈ

ኢሳት (ጥር 29 ፥ 2009)

የፌዴራሉ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የአርበኞች ግንቦት ሰባትን ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሲያቀኑ በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉ ስድስት የአየር ሃይል አባላት ላይ ከሶስት እስከ 10 አመት የሚደርስ ጽኑ እስራት አስተላለፈ።
ከሳሽ አቃቤ ህግ በሰኔ 2007 አም ተከሳሾቹ የአየር ሃይልን በመክዳት ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ለመቀላቀል ወደ ኤርትራ ሊያመሩ ሲሉ ባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ እንደተያዙ በክሱ አመልክቶ እንደነበር ይታወሳል።
የቀድሞው የአየር ሃይል አባላት ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል የማፍረስ አላማ ይዘው በሽብር ድርጅት ውስጥ አባላት በመሆንና በሽብር ድርጊት ተግባር ላይ ለመሳተፍ በማሰባቸው የሚል ክስን አቅርቦ እንደነበርም በወቅቱ መዘገባችን አይዘነጋም።

ይሁኑ የክስ ሁኔታ ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤቱ በስድስቱ ተከሳሾች ላይ ከሶስት አመት እስከ 10 አመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ማስተላለፉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ፣ መ/አ ብሩክ አጥናዬ፣ መ/አ ዳኔኢል ግርማ፣ መ/አ ጋዘኸኝ ድረስ እንዲሁም አቶ ተስፋዬ እሸቴ እና አቶ ሰይፉ ግርማ ስድስቱ ተከሳሾች ናቸው።
ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያሉት መቶ አለቀ ተከሳሾች በ10 አመት አምስተኛና ስድስተኛ ተከሳሾች ደግሞ በሶስት አመት ከስድስት ወር እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ መወሰኑ ታውቋል።
ከተከሳሾቹ መካከል መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤና ስደተኛ ተከሳሽ ሰይፉ ግርማ በሃምሌ ወር በቂሊንጦ እስር ቤት ደርሶ ከነበረው የእሳት አደጋ እጃቸው አለበት ተብሎ ተደራራቢ ክስ ከተመሰረተባቸው በርካታ እስረኞች ጋር እንደሚገኙበትም ለመረዳት ተችሏል።
የፍርድ ውሳኔው ሰኞ በተላለፈበት ወቅት አንደኛ ተከሳሽ ከግንቦት ወር 2008 አም ጀምሮ በጨለማ ክፍል እንዲቆዩ መደረጋቸውንና ከቤተሰቦቻቸው ጋርም ተገናኝተው እንደማያውቁ ለችሎት አስረድተዋል።
ከእነዚህም በተጨማሪ በምርመራ ወቅት ከባድ ድብደባ ሲፈጸምባቸው መቆየቱንና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸምባቸው እንደነበር አቤቱታቸውን አሰምተዋል።

No comments:

Post a Comment