Friday, February 3, 2017

ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ይፈጸምብናል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ለተመድ ደብዳቤ ጻፉ

ኢሳት (ጥር 2009)

የአስችኳይ ጊዜ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ ጋዜጠኞች ይፈጸምብናል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስመልክቶ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደብዳቤ ጻፉ።
ከወራት በፊት ለእስር የተዳረጉት ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩና አናኒያ ሶሪ ለእስር በተዳረጉ ጊዜ በሽብርተኛ ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አድርጋችኋል ቢባሉም እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ አለመቻላቸውን በደብዳቤያቸው ማስፈራቸውን አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት ዘግቧል።
በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ ከቤተሰብ ጋር እንዳይገኛኑ ተደርገው ለብቻቸው ለሶስት ቀን በጨለማ ክፍል እንዲቆዩ ተደርገው እንደነበር ጋዜጠኞቹ በጽሁፋቸው አውስተዋል።

ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ይድረስልን ብለው በጻፉት ባለሁለት ገጽ ደብዳቤ የአለም አቀፉ ማህብረሰብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊትን በማድረግ በህገመንግስት የተቀመጡ ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብር ሃላፊነታቸው እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ላይ ሲሰሩ የነበሩት ሁለቱ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር በዋሉ ጊዜ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ጋር ግንኙነት አላችሁ የሚል አቤቱታ ቀርቦላቸው እንደነበር አስረድተዋል።
ይሁንና ለእስር የተዳረጉበት ምክንያት እስካሁን ድረስ ወደ ፍርድ ቤት አለመመራቱ ስጋት አሳድሮባቸው ኣንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኞቹ በአንድ አነስተኛ ክፍል ከበርካታ እስረኞች ጋር እንደሚገኙና ጉዳያቸው የአለም አቀፍ ማህብረሰብ ትኩረት እንዲሰጠው በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል።
በሃገሪቱ ያለው ያሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አደጋ ውስጥ መሆኑን የመለከቱት ጋዜጠኞቹ ለእስር ከመዳረጋቸው በፊት በተለያዩ ድረገጾች በኢትዮጵያ ስላለው የፖለቲካና ማህበራዊ ጉዳዮች ጹሁፎችን በተከታታይ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወቃል።
በጥቅምት ወር ተግባራዊ የተደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲሁም ጋዜጠኞችና የፓርቲ አመራሮች ለእስር ተዳርገው ይገኛል። ከሶስት ወር በፊት ለእስር ከተዳረጉት ጋዜጠኞች በተጨማሪ የፓርቲ አመራር የሆነው አቶ ዳንዔል ሺበሺ በተመሳሳይ ሁኔታ ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።
በርካታ አለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መደረግን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ወደ 1ሺ የሚጠጉትም በመንግስት የጸጥታ አባላት መገደላቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።
መንግስት በበኩሉ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የክልል ከተሞች በተካሄደው ዘመቻ ከ24ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውንና ወደ ዘጠኝ ሺ የሚደርሱትም ከስልጠና በኋላ መለቀቃቸውን አረጋግጧል።

No comments:

Post a Comment