Monday, October 31, 2016

በኢትዮጵያ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንድ ሺህ ያህል ሰው መገደሉን የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ አስታወቀ


ኢሳት (ጥቅምት 21 ፥ 2009)
ለአንድ አመት ያህል በዘለቀውና በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል በቀጠለው ግድያ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንድ ሺህ ያህል ሰው መገደሉን የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ አስታወቀ።
ድርጅቱ ዕሁድ ጥቅምት 20 ቀን 2009 እንዳስታወቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 1ሺ ሲደርስ 40ሺ ሰዎች ደግሞ ታስረዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኦሮሚያ ክልል ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ አባብሶታል በማለት ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጥሪ ያቀረበው የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ፣ በሶስት ሳምንት ውስጥ የተገደሉት ሰዎች 1ሺ ሰዎች ስለመድረሳቸው ያገኘውን መረጃ ለማረጋገጥ መቸገሩን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም የግንኙነት መስመሮች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሙሉ በሙሉ በመቋረጣቸው የተከተለ መሆኑን አስረድቷል። የግንኙነት መስመሮቹ መቋረጥ በኦሮሚያን በአማራ ክልሎች እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ለመደበቅ እንደሆነም አመልክቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ከተካሄደውና 1ሺህ ሰዎች ከተገደሉበት ዕርምጃ የ248 ሟቾች አድራሻን በመግለጫው ያመለከተው የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ፣ ከ40 ሺህ ያህል እስረኞች የ3ሺህ 708ቱን አድራሻ አመልክቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆችን ተከትሎ በተካሄደው የመንግስት ሃይሎች ዕርምጃ፣ በሻላና አጄ ብቻ 85 እንዲሁም በአርሲ ነገርሌ 70 ሰዎች መገደላቸውን አስፍሯል።
የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት ሊግ ይህንን የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ም/ቤት፣ ለመንግስታቱ ማህበር የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና ለአፍሪካ ህብረት አስታውቋል።

No comments:

Post a Comment