Sunday, October 2, 2016

በዛሬው የኢሬቻ በዓል በተፈጠረው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠር ህይወት መጥፋቱን ኦፌኮ አስታወቀ

1451በዛሬው ዕለት በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ ኃይቅ ለመከበር በዝግጅት ላይ የነበረውና ከኦሮሞ ክብረ በዓሎች አንዱ የሆነው ኢሬቻ በዓል መንግሥትን በተቃወሙ ወጣቶችና በመንግሥት ታጣቂዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ተቋርጦ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አስታወቀ። የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፤ ፓርቲያቸው ባጠናቀረው መረጃ ሰዎች በተኩስ፣ በአስለቃሽ ጭስ እና በመረጋገጥ ሕይወታቸው እንዳለፈ ነው። 
በርካታ የቆሰሉ ሰዎች አሁንም በሆስፒታል እንደሚገኙ አክለው የተናገሩት ዶ/ር መረራ የሟቾች ቁጥር አሁንም ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው በቦታው የነበሩ የዐይን እማኞች ግጭቱ የተጀመረው በበዓሉ መክፈቻ ላይ ንግግር ሊያደርጉ የነበሩ ሰዎች ላያ እና ሊሰቀል በነበረው ባንዲራ ላይ ተቃውሞ በመነሳቱ ነው።
ከግጭቱም በኋላ በርካቶች በተኩስ፣ በአስለቃሽ ጭስ፣ በመረጋገጥ እና ገደል ውስጥ ገብተው ሕይወታቸው እንዳለፈ ተናግረዋ። የተጎዱ ሰዎችን በተመለከተ እስካሁን ይህ ነው የተባለ ትክክለኛ ቁጥር ማግኘት ባይቻልም የዐይን እማኞች ተጎጂዎች 25 በሚሆኑ መኪኖች ሲወሰዱ ተመልክተናል ብለዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በሰጠው መግለጫ፤ “የኢሬቻ በዓልን ባህላዊ አከባበር ጠብቆ ለማክበር የኦሮሞ ህዝብ አባገዳዎችና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ያደረጉት ሰፊ ቅድመ ዝግጅት በሁከት ፈጣሪ ኃይሎች ተስተጓጉሏል፡፡ ሁከት ፈጣሪዎቹ ባስነሱት ሁከት በተፈጠረ ግርግር በመረጋገጥ የሰው ህይወት ጠፍቷል፡፡” ብሏል። ዝርዝሩን ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ይጠብቁ። (ፎቶ፡ አንዷለም ሲሳይ)

No comments:

Post a Comment