Monday, October 10, 2016

“የቢሾፍቱ እልቂት ከደረሰ በሁዋላ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአጋዚ ወታደሮች ተገድለዋል”

መስከረም ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢትዮጵያውያንንና የአለምን ህዝብ ድንጋጤ ውስጥ የከተተው የቢሾፍቱ እልቂት ከተከሰተ በሁዋላ የተነሱ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን ለማፈን የአጋዚ ወታደሮች በወሰዱት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውን ከተለያዩ አካባቢዎች የኢሳት ወኪሎች ያሰባሱበዋቸው መረጃዎች አመልክተዋል።
ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞ በተካሄደባቸው በምስራቅ ሸዋና በምዕራብ አርሲ እልቂቱ ከፍተኛ እንደነበር ወኪሎቻችን ገልጸዋል።

በሊበን ዝቋላ ወረዳ ለተከታታይ 5 ቀናት በተደረገው ህዝባዊ ትግል 29 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። ተቃውሞው በወረዳው ዋና ከተማ አዱላላ እና የወ/ሮ አዜብ መስፍን እንደሆነ በሚነገርለት የመስኖ ስራና የከብት ማደለቢያ ቦታ ሲሆን፣ በተለይ አርብ እለት አርሶአደሮች ባስነሱት ተቃውሞ አጋዚዎች ከአርሶአደሮች ጋር የተኩስ ለውውጥ አድርጓል። እስር ቤቱን በማቃጠል እስረኞችን ያስፈቱ ሲሆን፣ ከ90 በላይ የጦር መሳሪያዎችን በመውሰድ ወታደሮችን ገድለዋል።
ተቃውሞው ከቁጥጥር ውጭ የሆነበት ገዢው ፓርቲ ተጨማሪ የአጋዚ ወታደሮችን በማሰማራት የጅምላ ግድያ ፈጽሟል።
አብዛኛው ህዝብ ጫካ ውስጥ መግባቱን የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ አካባቢው በአገር ሽማግሌዎች እየተዳደረ ነው መሆኑንም ገልጸዋል።
በሊበን ቅዳሜ ሩግቻ በምትባል ቀበሌ ደግሞ አማራዎችንና ኦሮሞችን ለማጋጨት የሞከረው ግጭት ከሽፎ አማራውና ኦሮሞው በአንድነት ተቃውሞውን ሲያሰማ ሰንብቷል። በአካባቢው ያሉ መንገዶችን አሁንም ደረስ ተዘግተዋል።
በአርሲ ነገሌ በተለያዩ ቦታዎች በተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ደግሞ ከመቶ በላይ ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ሄረሮ ላይ ባለፈው ቅዳሜ ደግሞ ህዝቡ አትግደሉን በማለት ወደ አደባባይ ሲወጣ አጋዚዎች በወሰዱት እርምጃ 23 ሰዎች ተገድለው አስከሬናቸው ከስንዴ ማሳ ማሀል ተገኝቷል።
ከአርሲ ነገሌ 48፣ አጄ፣ ቡራና ሻላ 30 የተገደሉት በየቀኑ ከሚገደሉት አንዳንድ ሰዎች ጋር ሲደማመር ከመቶ በላይ መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎች ፣ በዚሁ አካባቢ በወላይታና ኦሮሞ መካከል ግጭት ለመፍጠር መሞከሩን ገልጸዋል ። በመላ አገሪቱ የሚታየው ውጥረት ያሰጋው አገዛዙ ለ6 ወራት ወይም ከዚያ በላይ ሊቆይ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል።

No comments:

Post a Comment