Tuesday, January 24, 2017

በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተው የድርቅ አደጋ የከፋ እንደሆነ የአለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ

ኢሳት(ጥር 16 ፥ 2009)
በኢትዮጵያ ዳግም የተከሰተው የድርቅ አደጋ በ120 ወረዳዎች ውስጥ የከፋ እየሆነ መምጣቱን የአለም ምግብ ፕሮግራም (FAO) ይፋ አደረገ።
ካላፈው ሃምሌ ወር ጀምሮ በአራት ክልሎች የተከሰተው ይኸው የድርቅ አደጋ ሃገሪቱ በምግብ ምርት ራስን ለመቻል እያደረገች ባለው ጥረት ላይ ስጋት አሳድሮ እንደሚገኝ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ስላለው የድርቅ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

ድርቁ የከፋ ጉዳት እያደረሰባቸው ካሉት 120 ወረዳዎች መካከል 86ቱ ለሶስተኛ ተከታታይ አመታት የችግሩ ተጋላጭ በመሆናቸው ልዩ ክትትል የሚሹ ሆነው መለየታቸውን የአለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከጥቂት ወራቶች በፊት ጀምሮ በሃገሪቱ በድጋሚ የተከሰተው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ ሊሄድ እንደሚችል ትንበያን አስቀምጦ እንደነበር ይታወሳል። የድርቁ መባባስን ተከትሎ በኦሮሚያና በሶማሊ ክልሎች ስር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ወደ 600 አካባቢ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን መንግስት ይፋ አድርጓል።
በአራት ክልሎች ተከስቶ ያለው ይኸው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ በመሄድ ላይ መሆኑን የገለጸው የአለም ምግብ ፕሮግራም፣ በደቡብና ደቡባዊ ምስራቅ የሚገኙ የሃገሪቱ አካባቢዎች ክፉኛ ጉዳት እየደረሰባቸው መሆኑን በሪፖርቱ አስፍሯል።
ከወራት በፊት መጣል የነበረበት ዝናብ በወቅቱ አለመጣሉና በተለያዩ ሃገራት ተከስቶ ያለው የአየር ለውጥ አዲስ ለተከሰተው የድርቅ አደጋ ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል።
ይሁንና በኢትዮጵያ ባለፈው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ የነበረው ድርቅ ሙሉ ለሙሉ ዕልባት ሳያገኝ ተጨማሪ አደጋ ማጋጠሙ በሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦቱ ላይ ችግር መፍጠሩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል።
በኦሮሚያ ሶማሌ አፋርና ደቡብ ክልሎች ስር በሚገኙ የተለያዩ ዞኖች ውስጥ የተከሰተው የድርቅ አደጋ ባለፉት ጥቂት ወራቶች ብቻ በብዙ ሺዎች የሚቆጠር የቤት እንስሶች ህይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ ድርቁ አፋጣን ርብርብ ካልተደረገላት የከፋ ጉዳት ያስከትላል ተብሎ ተሰግቷል።
መንግስት በበኩሉ በምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸውን የቤት እንስሳት ለመታደግ የእንስሳት መኖ ወደ አካባቢው እንዲጓዝ መደረጉን አስታውቋል።
ይኸው የድርቅ አደጋ በ5.6 ሚሊዮን በሚሆኑ ሰዎች ላይ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጸው መንግስት፣ የአለም አቀፍ ማህበረሰብ እርዳታን እንዲያደርግ ጥሪውን አቅርቧል። ድርቁን ለመከላከል ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንደሚያስፈልግ መንግስትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጋራ አስታውቀዋል።

No comments:

Post a Comment