Tuesday, February 3, 2015

ሰበር ዜና የአንድነት አባላት በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን ተቀላቀሉ!!

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድና ኢህአዴግ በወሰኑብን ፖለቲካዊ ውሳኔ ምክንያት አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ተነጥቀናል ያሉ የአንድነት ፓርቲ አባላት› በይፋ ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስታወቁ፡፡

በእነ በላይ ፍቃዱ አመራርነት አንድነት ፓርቲን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ሲመሩ የነበሩ አመራሮች ዛሬ ጥር 26 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ከቀድሞ ፓርቲያቸው አንድነት ጋር የፕሮግራምም ሆነ የስትራቴጂ ተመሳሳይነት ወዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ተቀላቅለው ሰላማዊ ትግላቸውን ለመቀጠል መወሰናቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

መግለጫውን የ‹ቀድሞው አንድነት ፓርቲ› አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ አበበ አካሉ፣ ምክትል አፈ ጉባዔው አቶ ፀጋዬ አላምረው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፋረደኝ እንዲሁም የወጣቶች ጉዳይ ኃላፊው አቶ ስንታየሁ ቸኮል ሌሎችን በመወከል ሰጥተዋል፡፡



‹‹የምናምነው በሰላማዊ ትግል ብቻ ነው፡፡ ይህን ሰላማዊ ትግል ለመምራት ደግሞ ሰማያዊ ፓርቲ ብቁ ነው ብለን በማመን ፓርቲውን ተቀላቅለናል›› ብለዋል በመግለጫው ላይ የተወከሉት አዲሶቹ የሰማያዊ አባላት፡፡ በዚህ መሰረትም በርከት ያሉ አመራሮችና አባላት በይፋ የሰማያዊ ፓርቲ የአባልነት ፎርም ሞልተዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የአንድነት አባላት ሰማያዊ ፓርቲን መቀላቀላቸውን አስመልክቶ መግለጫ ለመስጠት ወደ ሰማያዊ ቢሮ ባቀኑበት ወቅት ፖሊስ ሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ ድረስ በመግባት ‹‹በሰማያዊ ስም መግለጫ የሚሰጡ አካላት እንዳሉ ሰለሰማን ነው›› በሚል ለፓርቲው አመራሮች ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡

Negere Ethiopia

ተጨማሪ ዜና

‹‹ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ አንድነትንና ሰማያዊን አዋህደዋቸዋል››

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት

የአንድነት መዋቅር በጣም ብዙ ነው፡፡ በየ ክፍለሀገሩ (በጎንደር፣ በወሎ፣ በጎጃም፣ በደቡብ ኢትዮጵያና በሌሎቹም) ለምዝገባ በተንቀሳቀስንበት ወቅት አብዛኛዎቹ በብዙ መንገድ ተባባረውናል፣ በግልጽም ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር እየሰሩ ነው፡፡ ብዙዎቹም እኛ በሌለን ቦታ ላይ የሰማያዊ ፓርቲን ፎርም ሞልተው ቀድመው ተመዝግበዋል፡፡ ይህን ስል ደግሞ ሰማያዊ በህግ ይህን የማድረግም መብት ስላለን ነው፡፡

የሰማያዊ ስራ አስፈጻሚ አንድ አባል ሙሉ አባል ለመሆን 6 ሳምንት መጠበቅ አለበት የሚለው አስፈላጊ ነው ብሎ ሲያምን ይህን በአንድ ቀን ውስጥ አባል የማድረግ ስልጣን አለው፡፡ በዚህ ደንባዊ አካሄድ የአንድነት አባላት በኢህአዴግና በምርጫ ቦርድ በፓርቲያቸው ላይ ባደረሰባቸው ችግር በአንድ ቀን አባል እንዲሆኑ ወስነናል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ከእነ በላይና ተክሌም ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ውይይት አድርገንበታል፡፡ የአንድነት አባላት በግል መጡ የሚባለው ለህግ ሲባል እንጅ ብዙዎቹ የአንድነት አባላት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ከዛሬ ቀደም ብለው ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር አብረው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ነገር ለበጎ ነው ይባላል፡፡ እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች እንዴት እርስ በእርሳቸው ይወዳደራሉ? ተመሳሳይና ተቀራራቢ ፕሮግራም እያላቸው ለምን አንድ አይሆኑም? እየተባለ ከህዝቡም ከጋዜጠኞችም ጥያቄ ሲመጣ ቆይቷል፡፡ በአንድ በኩል ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚዎችን አዳከምን ብለው በአንድነት ላይ ውሳኔ ሲያስተላልፉ ሁለቱን አንድነትና ሰማያዊን አዋህደዋቸዋል ማለት እችላለሁ፡፡

ከዚህም በኋላ ሰማያዊ እነሱን የሚያሳትፍ አመራር በመፍጠር በምክር ቤትም፣ በስራ አስፈጻሚም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ችሎታቸውና ብቃታቸው መሰረት በማድረግ እንዲሰሩ የሰማያዊ አመራር ክፍት መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ፡፡ የአንድነት አባላት በብቃታቸው በየቦታው ተመድበው እንዲሰሩ አስፈላጊውን ሁሉና ቀናነት ያለው አመራር እንደምናደርግ ይህን ትግል ለተቀላቀላችሁ አባላት ቃል እገባለሁ፡፡


No comments:

Post a Comment