Sunday, February 15, 2015

በደቡብ ወሎ ቃሉ ወረዳ ለሰማያዊ ፓርቲ እጩዎች መታወቂያ እድሳት ያደረገው የሀርቡ ከተማ 01 ቀበሌ ስራ አስኪያጅ ማህተምና ሌሎች ዶክሜንቶችን እንዲያስረክብ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጠው፡፡

በደቡብ ወሎ የቃሉ ወረዳ የክልልና የፌደራል እጩዎች ለምርጫ ቦርድ ማስረጃቸውን ሊያስገቡና ለማሳወቅ ወደምርጫ ቦርድ በሄዱበት ወቅት የመታወቂያ እድሳት እንደሚያስፈልጋቸው በተገለፀላቸው መሰረት ወደሚኖሩበት ሀርቡ ከተማ 01 ቀበሌ በመሄድ መታወቂያቸውን አሳድሰው ይመለሳሉ፡፡ ይህ በተደረገ በሁለተኛው ቀን መታወቂያውን ያደሰውን ቴድሮስ የተባለ የቀበሌው ስራ አስኪያጅ በቀበሌው ካድሬዎች ተጠርቶ ‹‹መታወቂያ ለተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች አድሰሀል፤ …..አንተ ባታድስላቸው ኖሮ እጩ ማሳወቂያው ቀን ሊጠናቀቅ የቀረው አንድ ቀን በመሆኑ ላይመዘገቡ ይችሉ ነበር፤ …..ስለዚህ ተቃዋሚዎችን በመርዳትህና በመተባበርህ፤ በቀጣይነትም በሀላፊነት ለመስራት እምነት ስለማይጣልብህ ማህተምና ሌሎች ሰነዶችን ባስቸኳይእንድታስረክብ ›› መባሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህን ተከትሎ እርምጃው የተወሰደበት ስራ አስኪያጅ ‹‹ ግለሰቦቹ መታወቂያ የማግኘት የዜግነት መብት አላቸው፤ ከአሁን በፊት ደግሞ የሰጣችኋቸውን ነው ያደስኩት፤ …..ይህ እኔን ሊያስጠይቀኝ የሚገባ ድርጊት አይደለም፤ህግን አክብሬ ነው የሰራሁት›› ሲል የተከራከራቸው ቢሆንም፤ ካድሬዎች አሻፈረኝ ብለዋል፡፡ ካድሬዎች በቃል የሰጡትን ምክንያት ግን በፅሁፉ ላይ ሳያሰፍሩ ለግለሰቡ በፅሁፍ በደረሰው ማስጠንቀቂያ ላይ ‹‹ …..ሀላፊነትህን በሚገባ ለመወጣት ባለመቻልህ፤ማህተምና ሌሎች በእጅህ የሚገኙ መረጃዎችን እንድታስረክብ፤……›› የሚል ይዘት ያለው ሲሆን ይህም ካድሬዎች ለሽፋንነት የተጠቀሙበት ሴራ መሆኑን የእርምጃው ህጋዊ አካሄድ ያልተከተለ በመሆኑ ብቻ መረዳት ይቻላል፡፡ ግለሰቡ በአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ በሰራተኛው ዘንድ ተወዳጅና ህግን አክብሮ የሚሰራ መሆኑን ከአካባቢው ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በመስሪያ ቤት በኩልም ምንም አይነት የፅሁፍም ሆነ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት የማያውቅ ምስጉን ሰራተኛ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑ፤ ስራ አስኪያጁ እስካሁን ድረስ…… ‹‹ማህተምም ሆነ ምንም ነገር አላስረክብም፤በህግ የሚጠይቀኝ አካል ካለ ይጠይቀኝ፤ ይህ ካልሆነ ግን እኔ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አደርሰዋለሁ›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ለግለሰቡ የተሰጠው የፅሁፍ ማስረጃ በእጃችን እንደገባ የምናቀርብ መሆኑን እንገልፃለን፡፡


No comments:

Post a Comment