Wednesday, March 8, 2017

በሶማሌና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች በዘለቀው ግጭት ሚና የነበራቸው ሰዎች ለህግ እንዲቀርቡ ጥሪ ቀረበ

ኢሳት (የካቲት 29 ፥ 2009)

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ከአራት ወር በላይ በክልሉና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ወረዳዎች የዘለቀው ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላለፈ።
በሁለቱ ክልሎች የድንበር አካባቢ ያለው ግጭት ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑን ያወሳው ምክር ቤቱ፣ ከሁለቱም ክልሎች ችግሮቹ ተባብሰው እንዲቀጥሉ ሚና የነበራቸው የመንግስት መዋቅር አካላት ለህግ ኣንዲቀርቡም ጥሪን አቅርቧል።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በመንግስት ድጋፍ የሚደረግላቸው ታጣቂዎች ጥቃቱን እየፈጸሙ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።

እነዚሁ አካላት ለፍትህ እንዲቀርቡ ያሳሰበው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት በሰዎች ላይ ከደረሰው የህይወትና የንብረት ውድመት በተጨማሪ የሶማሌ ክልል ባንዲራን በኦሮሚያ ክልል የመትከል ዕርምጃን መፈጸሙን አስታውቀዋል።
መፍትሄን ያላገኘው ይኸው ግጭት በምስራቅ ሃረርጌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ወረዳዎች እንዲሁም በጉጂ ዞን መሆኑም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ገልጿል። የታጣቂዎች ዕርምጃ ግዛትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን የነዋሪዎችን ንብረት የመዝረፍ አላማ እንደነበረውም ፓርቲው አክሎ አስረድቷል።
በዚሁ ግጭት ዙሪያ በቅርቡ መግለጫን ያወጣው የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ በሁለቱም ወገን ከ400 የሚበልጡ ሰዎች መሞታቸውን በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ግጭቱ ዕልባት እንዲያገኝ ያስችላል ያለውን ባለሰባት ነጥብ ውሳኔን ያስተላለፈ ቢሆንም በጥቃቱ ስለሞቱ ነዋሪዎችና ስለደረሰው የንብረት ውድመት ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥቧል። በአምስት የኦሮሚያ አዋሳኝ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የቀጠለው ይኸው ግጭት የተለያዩ የሰብዊ መብት ጥሰቶች እንደተስተዋሉበትም የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት ችግሩ በኮማንድ ፖስቱ ዕልባት እንዲያገኝ ተደርጓል ቢሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ግጭት መቀጠሉን ለመገኛኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

No comments:

Post a Comment