Tuesday, March 21, 2017

በቆሼ በደረሰ አደጋ የሟቾች ቁጥር በመቶዎች ሊበልጥ እንደሚችል የጸጥታ አካላት ገለጹ

ኢሳት (መጋቢት 12: 2009)

በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ቆሼ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቆሻሻ መደርመስ (መናድ) በደረሰው አደጋ የሟቾች ቁጥር መንግስት ከሚገልጸው በመቶዎች ሊበልጥ እንደሚችል ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ የጸጥታ አካላትን ዋቢ በማድረግ ዘገበ።
ቁፋሮ እየተካሄደበት ባለው ስፍራ ለጸጥታ ስራ ተሰማርቶ የሚገኝና ማንነቱ እንዳይገለጽ የጠየቀ የጸጥታ ባልደርባ አሁንም ድረስ በርካታ ሰዎች ከቁፋሮ አለመውጣታቸውን ለጋዜጣው አስረድቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአንድ ሳምንት በላይ በዘለቀው ቁፋሮ የ113 ነዋሪዎችን አስከሬን ብቻ ሊገኝ መቻሉን ቢያሳውቅም፣ የጸጥታ አባሉ የሟቾች ቁጥር መንግስት ከገለጸው በመቶዎች ሊበልጥ እንደሚችል ለኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አስረድቷል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከቀናት በፊት ከ80 የሚበልጡ ሰዎች አሁንም ድረስ ሊገኙ አለመቻላቸውን ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁፋሮ ስራው ወደ መገባደድ ተደርሷል ቢልም የአካባቢው ነዋሪዎችና የቤተሰብ አባሎቻቸውን ማግኘት ያልቻሉ በርካታ ሰዎች ቁፋሮው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመጠየቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።
የከተማው አስተዳደርም ሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች አደጋው በደረሰ ጊዜ ምን ያህል ሰዎች በስፍራው ይኖሩ እንደነበር በቂ መረጃ የሌላቸው በመሆኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በትክልል ማወቅ እንዳልቻለ የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
ይሁንና ነዋሪዎችና የከተማው አስተዳደር 48 መኖሪያ ቤቶች በቆሻሻ ክምሩ መደርመስ ሙሉ ለሙሉ እንደወደሙ አረጋግጠዋል።
በእነዚሁ መኖሪያ ቤቶች በአማካይ በአንድ መኖሪያ ቤት በትንሹ ሰባት ሰው ይኖር እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።
ሰኞ በአደጋው ስፍራ የተገኘ የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘጋቢ አሁንም ድረስ በርካታ ሰዎች የቤተሰብ አባሎቻቸውን አስከሬን ለመፈለግ በቦታው እንደሚገኙ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment