Thursday, December 1, 2016

ዶ/ር መረራ ጉዲና ከእስር የሚፈቱበትን ሁኔታ እንዲመቻች ጥሪ ቀረበ

ኢሳት (ኅዳር 22 ፥ 2009)
የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ህብረቱ ለእስር በተዳረጉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ከእስር የሚፈቱበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጥሪ ማቅረባቸውን ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ሃሙስ ዘገበ።
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር መረራ በኢትዮጵያ ተደንግጎ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያን ተላልፈው ተገኝተዋል በሚል ረቡዕ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የፓርቲው አመራር ዶ/ር መረራ ከአንድ ሳምንት በፊት የአውሮፓ ህብረት ዋና መቀመጫ በሚገኝበት ብራሰልስ ተገኝተው ከህብረቱ የፓርላማ አባላት ጋር ውይይት ማካሄዳቸው ይታወሳል።

ከጉዟቸው መልስ ለእስር የተዳረጉት የኦፌኮ አመራሩ በብራሰልስ ቆይታቸው ከግንቦት ሰባት አመራር ጋር ተገናኝተው መግለጫን ሰጥተዋል ሲል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊነት የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት ሃሙስ አስታውቋል።
ይሁንና የዶ/ር መረራ ጉዲና መታሰርን ተከትሎ የአውሮፓ ፓርላማ አባል የሆኑት አና ጎሜዝ ለህብረቱ የውጭ ጉዳይ ክፍል አስቸኳይ ደብዳቤን በማቅረብ የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው ህብረቱ እርምጃን እንዲወስድ ጠይቀዋል።
የኦፌኮ አመራር ለእስር መዳረግ የሃገሪቱ መንግስት ህብረቱ በተደጋጋሚ ለሚያቀርበው የዴሞክራዊ መከበር ጥያቄ ትኩረትን የማይሰጥ እንደሆነ ማሳያ ነው ሲሉ የፓርላማ አባሏ በጻፉት ደብዳቤ አስፍረዋል።
የአውሮፓ ህብረት አሳሳቢ ነው ባሉት ጉዳይ ላይ አፋጣኝ ዕርምጃን የማይወስድ ከሆነ ድርጊቱ በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ ውጥረትና አለመረጋጋት ያባብሰዋል ሲል አና ጎሜዝ አክለው ገልጸዋል።
ከአውሮፓ ጉዞ መልስ በአዲስ አበባ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በቁጥጥር ስር የዋሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ የስቃይ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸውም የህብረቱ የፓርላም አባል በደብዳቤያቸው አመልክተዋል።
ዋሽንግተን ፖስት፣ እንዲሁም ቢቢሲና የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የኦፌኮ አመራር ለእስር መዳረግን በተመለከተ ዘገባዎች እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን፣ የዶ/ር መረራ ጉዲናና 2 የቅርብ የቤተሰብ አባላትም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
የፓርላማ አባሏ አና ጎሜዝ የህብረቱ የፓርላማ አባላት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ለመምከር ጋብዟቸው እንደነበር አውስተዋል።
መንግስት የዶ/ር መረራ ለእስር መዳርግን ቢያረጋግጥም ፍርድ ቤት ይቅረቡ አይቅረቡ የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።
በሃገሪቱ ተደንግጎ ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ተጠርጣሪዎች ለእስር ከተዳረጉ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የጊዜ ገደብ በሌለው ሁኔታ በእስር እንደሚቆዩ ይገልጻል። የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ ከ 11ሺ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን መንግስት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment