Wednesday, December 14, 2016

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 አመታት ወደ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገራት ተርታ እንደማትገባ ተመድ ይፋ አደረገ

ኢሳት (ታህሳስ 5 ፥ 2009)

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 አመታት ወደ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገራት ተርታ እንደማትገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይፋ አደረገ።
የመንግስት ባለስልጣናት ሃገሪቱ በቀጣዮቹ አስር አመራት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ትገባለች ሲሉ በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል። ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ ሰሞኑን ሪፖርቱን ያወጣው የድርጅቱ የንግድና የልማት ጉባዔ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ 16 ሃገራት እቅዱን እንደሚያሳኩ ቢገልጽም፣ ኢትዮጵያን ሳያካትት ቀርቷል።

ከአፍሪካ ሃገራት አንጎላ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሁን ካሉበት የዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እንደሚመደቡ የልማት ጉባዔው የአፍሪካ ቀጠና ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ጆይ ካቲዌክዋ ሪፖርቱ ከቀናት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ይፋ በተደረገበት ወቅት ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
በአለማችን ኢትዮጵያን ጨምሮ 48 ሃገራት በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ድረጃ ላይ ተመድበው የሚገኙ ሲሆን፣ አብዛኛው የሃገሪቱ ዜጎች በድህነት ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ ይፋ ባደረገችው የእድገትና የትራስፎርሜሽን እቅድ መሰረት ሃገሪቱ በቀጣዮቹ 10 አመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ እንደማትመደብ ትንበያውን አስቀምጧል።
የዕርስ በዕርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኘው የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ጅቡቲና፣ ኔፓል ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ይመደባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ሃገሪቱ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደመስፈርት የተቀመጠውን 1ሺ 35 ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ ለሶስት ተከታታይ አመታት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል።
እንዲሁም አንድ ሃገር ከዝቅተኛ ደረጃ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሃገራት ተርታ ለመመደብ 1ሺ 242 ዶላር ብሄራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ማስመዝገብ እንደሚጠበቅባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዝቅተኛ መስፈርትነት ካስቀመጣቸው መስፈርቶች ማካከል ይገኙበታል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ይህንን መስፈርት አታሟላም ሲሉ ዶ/ር ጆይ ለመገኛኛ ብዙሃን አስረተዋል። የነፍስ ወከፍ ገቢን ከማሳደግ በተጨማሪ የሰው ሃብት ልማትን ማሳደግ እንዲሁም የተመጣጠነ ምግብን ለዜጎች ማዳረስ በመስፈርትነት ተቀምጠዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደረጃ መስፈርቶቹን ካወጣ 45 አመታት ቢቆጠሩም እስካሁን ግን ካላደጉ 48 ሃገሮች ተርታ መውጣት የቻሉት አራት አገሮች መሆናቸው ታውቋል።
16 ሃገራት ደግሞ በቀጣዮቹ 10 አመታት ውስጥ ሽግግሩን ያሳካሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኢትዮጵያም በቀጣዮቹ አስር አመታት እንደማትደርስበት የተባበሩት መንግስታት አረጋግጧል።

No comments:

Post a Comment