Thursday, June 8, 2017

በኬንያ ህወገጥ የተባሉ 40 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ


ኢሳት (ሰኔ 1 ፥ 2009)
የኬንያ ፖሊስ ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉ 40 ኢትዮጵያውያን ሃሙስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ።
የኒጅሩ አስተዳደር ኮማንደር ፓርቲክ ምዋምባ ኢትዮጵያውያኑ በአስተዳደሩ ስር በምትገኘው የቃዬሌ ከተማ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ እንዳሉ በነዋሪዎች በተደረገ ጥቆማ ሊያዙ መቻላቸውን እንደገለጹ ዘስታር የተሰኘ የሃገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧልል።
በህገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ገብተዋል የተባሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ ከ10 እስከ 25 አመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ መሆናቸው ታውቋል።
ኢትዮጵያውያን ስደተኞቹ በአንድ ወኪል አማካኝነት ሰኞ ከኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ደቡብ አፍሪካ የማቅናት ዕቅድ እንደነበራቸው በአስተርጓሚ በኩል ቃል እንደሰጡ የንጅሩ አስተዳደር ሃላፊ አስረድተዋል።

የኬንያ ፖሊስ ምንም የጉዞ ሰነድ አልያዙም በተባሉ ኢትዮጵያውያን ላይ ምርመራ መጀመሩን በመግለፅ ወኪል የተባለውን አካል  ለመያዝ ፍለጋ እያካሄደ እንደሚገኝ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት በቃየሌ ከተማ በሚገኝ አንድ እስር ቤት በእስር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውን በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኬንያ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ወደ ሃገሪቱ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውን ቁጥር መጨመርን ተከትሎ በድንበር አካባቢ አዳዲስ የቁጥጥር ኬላዎችን ቢያቋቁሙም የስደተኞችን ፍልሰት ሊቀንስ እንደሚችል ተገልጿል።
የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) በየዕለቱ በትንሹ ወደ 30 ኢትዮጵያውያን  ወደ ኬንያ እንደሚሰደዱ አስታውቋል። ከሃገሪቱ በመሰደድ ላይ ያሉት ኢትዮጵያውያን ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ወደ ተለያዩ ሃገራት የመሰደድ ዕቅድ እንዳላቸው ታውቋል።
ከአንድ አመት በፊት በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ወጣት በመሰደድ ላይ መሆኑን የድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።
ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ላይ ያሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ኬንያን ጨምሮ በተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው ለእስር ተዳርገው ይገኛሉ።
የኬንያ፣ ማላዊ፣ ታንዛኒያ፣ እንዲሁም የሞዛምቢክ መንግስታት የኢትዮጵያውያን ስደት እየተበራከተ መምጣቱን ሲገልፅ ቆይተዋል።
በማላዊ ብቻ ከ100 የሚበልጡ ኢትዮጵያን በእስር ቤት የሚገኙ ሲሆን፣ የሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ኢትዮጵያውያኑ የተላለፈባቸውን የእስር ቅጣት ጨርሰው በእስር ቤት በመሰቃየት ላይ መሆናቸው ተገቢ አይደለም ሲሉ ስደተኞቹ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ዘመቻ ከፍተዋል።
የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት (IOM) በበኩሉ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ የገንዘብ ድጋፍ እያሳሰበ መሆኑን ይገልጻሉ።

No comments:

Post a Comment