Wednesday, June 14, 2017

በለንደን ከተማ በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ አደጋ 12 ሰዎች ሞተው 68 ሌሎች ቆሰሉ

ኢሳት (ሰኔ 7 ፥ 2009)
በእንግሊዝ አገር በምዕራብ ለንደን ከተማ በአንድ ህንጻ ላይ በተከሰተ የእሳት ቃጠሎ 12 ሰዎች መሞታቸውንና 68 ሌሎች ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገለጸ። በአደጋው የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተሰግቷል።
በለንደን የ24 ፎቅ ርዝመት ባለው ግሬንፈል ታወር መኖሪያ ህንጻ ላይ የእሳት ቃጠሎ የተከሰተው ነዋሪዎቹ ተኝተው በነበረበት ረቡዕ እኩለ ሌሊት ላይ መሆኑን የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል። 
በህንጻው ላይ ቃጠሎው በተከሰተበት ሰዓት ብዛት ያላቸው ነዋሪዎች በመስኮት በመሆን እርዳታ እየጠየቁ እንደነበር የአልጀዚራ የዜና ወኪል ከስፍራው ዘግቧል።

በህንጻው ላይ የተቀጣጠለውን እሳት ለማጥፋት የለንደን የእሳት አደጋ ብርጌድ 40 የእሳት ማጥፊያ ሞተሮችንና (መኪኖችንና) 200 የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ማሰማራቱ የለንደን ከተማ የእሳት አደጋ መከላከል ዲፓርትመንት ባለስልጣናት ገልጸዋል።
የእሳት ቃጠሎው ከሁለተኛ ፎቅ የጀመረ ሲሆን፣ ወደ ላይ ሁሉንም የመኖሪያ አፓርትመንቶች ማቃጠሉ ታውቋል። ይህም የህይወት ማዳን ስራውን ለመስራት አስቸጋሪ እንዳደረገው ለማወቅ ተችሏል።
ህንጻው ሙሉ ለሙሉ መውደሙን የገለጹት የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን፣ ከህንጻው እየፈራረሰ የሚወርደው ፍርስራሽ ለእሳት አደጋ ሰራተኞች ፈተና እንደሆነባቸው የለንደን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
በህንጻው ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች ለተለያዩ ጉዳቶች ተዳርገው ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን እነዚሁ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የግሬንፌል ህንጻ ነዋሪዎች ከዚህ በፊት በህንጻው ውስጥ እሳት ሊነሳ ይችላል በሚል ስጋታቸውን ለአስተዳደሩ ሲገልጹ ቢቆዩም፣ የህንጻው አስተዳደር የነዋሪዎችን ስጋት በቸልታ በማለፉ አደጋ መድረሱ ተገልጿል።

No comments:

Post a Comment