Thursday, November 17, 2016

በአባይ ግድብ አካባቢ ያለው የስራ እንቅስቃሴ መዳከሙን ጋዜጠኞች ገለጹ ።

ኅዳር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ‹‹ በአባይ ግድብ ላይ ያለው እንቅስቃሴ ቆሟል የሚል ወሬ በስፋት እየተወራ ነውና ወሬውን አክሽፉ!” ተብለው ለጉብኝት የተላኩት ጋዜጠኞች ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴ ባለማየታቸው የሚወራው ትክክል መሆኑን አረጋጋጥው መመለሳቸውን ለኢሳት ገለጹ።
ሰሞኑን ወደ አባይ ግድብ የተላከው የ መንግስት ጋዜጠኞች ቡድን ለጉብኝት በቆየበት አንድ ቀን፤ ምንም አይነት ስራ ሲሰራ አለመመልከቱን ገልጿል፡፡ ‹‹ ለአንድም ደቂቃ ስራው አይስተጓጎልም ›› የተባለለት ይህ የግድብ ስራ አልፎ አልፎ ከሚንቀሳቀሱ ተሸከርካሪዎች በስተቀር ምንም አይነት የስራ እንቅስቃሴም ሆነ ሰራተኞችን አለመመልከቱንና ስራው ተስተጓጉሏል የሚለው እውነት መሆኑን የቡድኑ አባላት ተናግረዋል።

ከአሁን በፊት ለጉብኝት በተጓዙ ጊዜ የነበረው የሰራተኞች እንቅስቃሴ፣የማሽኖች ጩኸትና ሩጫ በአሁኑ ሰዓት የሌለ መሆኑን የገለጹት ጋዜጠኞች ፤ወደ ግድቡ ከገቡበት ሰዓት ጀምሮ ጉብኝቱን አጠናቀው እስኪወጡ ድረስ አንድም የስራ እንቅስቃሴ አልተመለከቱም፡፡ የግድቡን እንቅስቃሴ ያስጎበኟቸው አንድ ባለሙያ ብቻ ሲሆኑ ፣ በግድቡ ውስጥ ያዩዋቸውን አንዳንድ ሰራተኞች አስተያየት ለመቀበል ቢጠይቁም፣ አስጎብኝው የቀረበውን ጥያቄ እንደማይቀበሉት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በግቢው ውስጥ ከግማሽ ቀን በላይ የተዘዋወሩት ጎብኝ ጋዜጠኞች አንድ ሰራተኛ ለማነጋገር ቢሞክሩም እርሱም ‹‹ ምንም መረጃ እንዳንሰጥ ታግደናል፡፡ስልክም እንዳናወራ ሁላችንም ስልካችንን ዘግተናል፡፡ እባካችሁ ከናንተ ጋር ከታየሁ ችግር ይፈጠርብኛል ›› በማለት ጋዜጠኞች ግራ እስኪጋቡ ድረስ ፈጥኖ እንደተለያቸው ተናግረዋል፡፡
‹‹ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎችን ሊገልጹ የሚችሉት የግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኛው ብቻ ናቸው ›› የሚል ምላሽ ያገኙት ጋዜጠኞች፣ ከኢንጂነሩ የተብራራ ምላሽ እናገኛለን በማለት ቢያስቡም ያሰቡት አልተሳካላቸውም።
ኢንጂነሩ ምንም ዓይነት ጥያቄ እና መልስ እንደማያስፈልግ በመናገር ግድቡ አሁን የደረሰበትን አጠቃላይ ገጽታ በአጭሩ ካስረዱ በሁዋላ፣ ‹‹ጋዜጠኞች ይህን ግድብ በተደጋጋሚ ስለተመለከታችሁት ከአሁን በኋላ የተመለከታችሁትን በራሳችሁ መግለጽ ትችላላችሁ፡፡ከአሁን በኋላ አስጎብኝ አያስፈልጋችሁ፡፡መልካም ጉዞ ይሁንላችሁ ›› በማለት እንዳሰናበቱዋቸው ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የግደቡ ሰራተኞች ህዝባዊ ትግሉን ትደግፋላችሁ ተብለው እየተያዙ በመታሰራቸው እና ተፈላጊ የተባሉትም አካባቢውን ለቀው ከመጥፋታቸው ጋር በተያያዘ ስራው ሳይጓተት እንዳልቀረ ጋዜጠኞች ግምታቸውን ተናግረዋል። በገንዘብ እጥረትም ስራው ሊጓተት እንደሚችል አስተያየታቸውን ገልጸዋል።
በቅርቡ ኢሳት በአካባቢው የሚገኘው የንግድ ባንክ ም/ል ሃላፊን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መጥፋታቸውን፣ ከ30 በላይ የሳሊኒ ፣ የሜቴክና ሌሎችም ኩባንያ ሰራተኞች ተይዘው መታሳራቸውን ዘግቦ ነበር።

No comments:

Post a Comment