Wednesday, April 19, 2017

በሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከቀናት በፊት በሶስት ወረዳዎች አዲስ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ

ኢሳት (ሚያዚያ 11 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የደቡብ ሱዳን ሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል የሚፈጽሙትን ጥቃት ለመከላከል በአካባቢው እንደሰፈረ መንግስት ቢገልጽም፣ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከቀናት በፊት በሶስት ወረዳዎች አዲስ ጥቃት ፈጸሙ።
ቁጥራቸው ያልታወቀው የጎሳ ታጣቂዎች መጋቢት 25 እና ሚያዚያ 1 ቀን 2009 አም የኢትዮጵያ ድንበርን በመዝለቅ በጎድ ጆርና ዲማ ወረዳዎች ጥቃት ማድረሳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የእርዳታ ማስተባበሪያ መምሪያ አስታውቋል። ይሁንና የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቱ ታጣቂዎች በሶስት ወረዳዎች ያደረሱትን ጉዳት ከመግለጽ ተቆጥቧል።
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ባለፈው ወር በጋምቤላ ክልል ስር በሚገኘው የጎግና የጆር ወረዳዎች በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ 28 ኢትዮጵያውያንን መግደላቸውና 43 ህጻናትን አፍነው መውሰዳቸው ይታወሳል።

የጎሳ ታጣቂዎቹ የፈጸሙት ይህንኑ ጥቃት ተከትሎ የመከላከያ ሚኒስቴር የጸጥታ ሃይል በአካባቢው እንዲሰማራ መደረጉን አስታውቋል።
ይሁንና የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ የጋምቤላ ክልል ልዩ ፖሊስ እንዲሁም የመንግስት ሚሊሺያዎች ጥቃት በደረሰው አካባቢ እንዲሰማሩ ቢደረግም የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ከባለፈው ወር መጠነ ሰፊ ነው የተባለ በሶስት ወረዳዎች ጉዳት ማድረሳቸው ታውቋል።
የዲማ ወረዳ የአደጋ መከላከልና የምግብ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ፍርሃትና ስጋት ያደረባቸው በመሆኑ፣ የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው ለመሰደድ እንደወሰኑ ለተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ተቋም እንዳመለከቱም ለመረዳት ተችሏል።
በቅርቡ የጋምቤላ ክልል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ባለፈው ወር ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን ለማስለቀቅ መንግስት ቸልተኝነት አሳይቷል ሲሉ ቅሬታ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ከ1 ሺ የሚበልጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በሁለቱ ወረዳዎች በመጋቢት ወር ፈጽመውት በነበረው ጥቃት ታፍነው ከተወሰዱት ከ40 በላይ ህጻናት በተጨማሪ በርካታ የቤት እንስሳት መወሰዳቸንም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት ይገልጻሉ።
ከቀናት በፊት በሶስት ወረዳዎች የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ የፌዴራል መንግስት የሰጠው መረጃ የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ባለፈው ወር በጎጅ እና ጆር ወረዳዎች ተፈጽሞ በነበረው የታጣቂዎች ጥቃት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ 743 የቤተሰብ አባላት አሁንም ድረስ ለምግብና ምግብ ነክ ላልሆኑ ችግሮች ተጋልጠው እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በጋምቤላ ክልል አድርሰውት በነበረ ጥቃት ከ200 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ተገድለው ከ100 የሚበልጡ ህጻናት ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸውም አይዘነጋም።
መንግስት በደቡብ ሱዳን መንግስት በኩል ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ባካሄደው ድርድር ታፍነው ከተወሰዱት ህጻናት መካከል አብዛኞቹ መመለሳቸውን የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) መረጃ የመለክታል።

No comments:

Post a Comment