Wednesday, January 2, 2019

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጠ

ተቋሙ በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች፣ በሶማሌ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ክልል  የተፈጸመውን ወንጀል አስመልክቶ ተከሰቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ መነሻ ጉዳያቸውን ሲያጣራ ቆይቶ የምርመራ ሥራ መጠናቀቅን አስመልክቶ፣ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለህግ ታራሚዎች የተሰጠ ይቅርታ እንዲሁም የምህረት አዋጅ ሀገር አቀፍ አፈጻጸም ወቅታዊ መረጃ አሰመልክቶ ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ፡፡


መግለጫውን የሰጡት በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ፣ የተደጋጁና ድንበር ተሸጋሪ  ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ፍቃዶ ጸጋ እና የይቅርታ ቦርድ ዳይሬክተር አቶ ዘለቀ ዳለሎ ሲሆኑ በመግለጫው እንደገለጹት

"በኦሮሚያ ክልል በቡራዩና በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ አካባቢዎች ተከሰቶ የነበረው ሁከትና ብጥብጥ መነሻ ጉዳዮች ሲያጣራ ቆይቶ የምርመራ ሥራው መጠናቀቁን በመግለጽ በዚህ ወንጀል የተሳተፉ በአጠቃላይ #109_ሰዎች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 240/3/ በመተላለፍና በተደራራቢ ወንጀል ክስ የተመሰረተ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ #81ዱ በቁጥጥር ስር ውለው በማረሚያ ቤት ያሉ፣ #28ቱ እስካሁን በቁጥጥር ስር ያልዋሉ መሁኑን ተገልጿል፡፡

በሁከትና ብጥብጡ የደረሰ የጉዳት መጠን #37የሰው ሕይወት መጥፋት፣ #315_ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት፣ 17,538,744 /አስራ ሰባት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ስምንት ሺ ሰባት መቶ አርባ አራት/ ብር የሚገመት ንብረት መውደም እንዲሁም 4506 የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑን ይታወሳል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ #ለ538 የህግ ታራሚዎች #ይቅርታ እንደሚሰጥ ጠቁመው በተሰጠው ይቅርታ በአመዛኙ ህጻናት ልጆችን ይዘው በማረሚያ ቤት ለሚገኙ እናቶች፣ የጤና ችግር ላለባቸውና ለማረን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ፣ እድሜያቸው ከ60 በላይ ለሁኑ እንዲሁም በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መልካም ስነምግባር ላሳዩና የቆይታቸውን 1/3 ጊዜ ላሳለፉ ታራሚዎች እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

የምህረት አዋጅ ቁጥር 1096/2010 ከሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም ወጥቶ በሥራ ላይ መዋሉን በማስታወስ በዚሁ መሰረት እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ 13,122 ግለሰቦች ተጠቃሚ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

#የፌደራል_ጠቅላይ_አቃቢ_ህግ

No comments:

Post a Comment