Wednesday, November 7, 2018

ዓለም አቀፉ የቡና ቱሪዝም ፕሮግራም ተቃውሞ አስነሳ

(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 28/2011) የቡና መገኛ ጂማ ነው በሚል በቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን የሚከበረው የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የቡና ቱሪዝም ፕሮግራም ተቃውሞ አስነሳ።

ዛሬ በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ህዝቡ አደባባይ በመውጣት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አውግዟል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቡናና ሻይ ባለስልጣን ጋር በመተባባር የዘንድሮውን የቡና ቱሪዝም ለማክበር በከፋ የተያዘው ፕሮግራም ተሰርዞ በጂማ እንዲሆን መደረጉ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭና ታሪክን የሚቀማ ተግባር ነው ሲል የከፋ ዞን አስተዳደር ቅሬታውን ገልጿል።

በቦንጋ ከተማ እየተደረገ ባለው ተቃውሞ ምክንያት ከቦንጋ ወደ ጅማ እና ሚዛን የሚወስዱ መንገዶች መዘጋታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን ጋር በየዓመቱ የሚከበረውን የቡና ቱሪዝም ቀን በካፋ ዞን የቡና መገኛ ቦታ በሆነው አከባቢ እንዲሆን ዝግጅት እያደረገ ነበር።
ፕሮግራሙን በተመለከተም ይፋዊ የሆነ መግለጫ በመስጠት ካፋ ዞን እንገናኝ የሚል ማስታወቂያ በመልቀቅ ቅድመ ዝግጅት ላይ ነበር።
የካፋ ዞን ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በላከው የቅሬታ ደብዳቤ ላይ እንደተመለከተው በከፋ ዞን ይደረጋል የተባለው የዘንድሮው የቡና ቱሪዝም ቀን ቀርቷል።
ምክንያቱ ባይገለጽም በምትኩ የቡና መገኛ በሆነው በጂማ ፕሮግራሙ እንደሚካሄድ የሚገልጽ መረጃ ነው ከአዘጋጆቹ የወጣው።
የካፋ ዞን አስተዳደር እንደገለጸው የቡና መገኛ ከፋ ዞን ማኪራ ቀበሌ ቡኒ መንደር ሆኖ ሳለ ታሪክን በመገልበጥ ጂማ የቡና መገኛ ተደርጎ መጠቀሱ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል።
አስተዳደሩ ጨምሮ እንዳስታወቀው ይህ ዓይነቱ የታሪክ ሽሚያ ብሔርን ከብሔር የሚያጋጭ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬን የሚፈጥር ተግባር ነው።
የካፋ ዞን ኮሚኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ጨምሮ እንዳስታወቀው በዓለም ደረጃ የሚታወቀውንና ከፋ የቡና መገኛ መሆኗን የሚመሰክረውን ታሪክ መሻር በህግ ከሚተዳደር መንግስታዊ ተቋም የማይጠበቅ ርምጃ ነው።
የኢትዮጵያ አየርመንገድና የቡናና ሻይ ባለስልጣን ህዝብ ከህዝብ የሚያጋጨውን ውሳኔያቸውን እንዲያስተካክሉና ፕሮግራሙ ቀድሞ በተያዘለት ትክክለኛ የቡና መገኛ ስፍራ እንዲከበር እንዲያደርጉ የከፋ ዞን ጠይቋል።
የዘንድሮ የቡና ቱሪዝም ቀን የሚከበርበት ቦታ ከካፋ ዞን ተቀይሮ በጂማ መደረጉን ተከትሎ በቦንጋ ከተማ ጠንከር ያለ ተቃውሞ መደረጉን የደረሰን ዜና ያስረዳል።
የቡና መገኛ ቦታ በኢትዮጵያ አየር መንገድና በቡናና ሻይ ባለስልጣን የተጠቀሰው ሆን ተብሎ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ነው በሚል የቦንጋ ነዋሪዎች መንገዶች በድንጋይ በመዝጋት መቃወማቸው ታውቋል።
በዚህም ከቦንጋ ወደ ጂማና ሚዛን የሚወስዱ መንገዶች ተዘግተዋል። የተጠናከረ ተቃውሞ ከሰሞኑም እንደሚኖር ከአከባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ኢሳት ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የጎሳ ፌደራሊዝሙ ያዋቀረው ክልላዊ አስተዳደር ለተፈጠረው ችግር ምክንያት ነው ብለዋል።
ከዚህ በፊት የቡና መገኛ ቦታ የተመለከተው ታሪክ በኢትዮጵያውያን መካከል የግጭት መንስዔ አልነበረም ያሉት መምህሩ እንዲህ ዓይነቱ የታሪክ ሽሚያ በቶሎ መፍትሄ ካልተሰጠው የከፋ ግጭት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በካፋ ዞን አስተዳደር በኩል የቀረበውን ቅሬታ በተመለከተ የኢትዮጵያ አየርመንገድም ሆነ የቡናና ሻይ ባልስልጣን እስከአሁን ምላሽ አልሰጡም።

No comments:

Post a Comment