Wednesday, March 2, 2016

ህወሓት “ከቡና ጠጡ” ወደ “መርዝ ጠጡ” ከታደሰ ብሩ

የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች ለሁለት ቀናት ያካሄዱት የሥራ ማቆም አድማ ከፍተኛ ዋጋ ያለው ትምህርት ሊገኝበት የሚገባ ነው። ስታሊናዊ አፈና በሰፈነባት አዲስ አበባ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱ አድማ መሞከሩ ብቻውን የሚያስደንቅ ሳለ ተግባራዊ ሆኖ ከተማዋን ለሁለት ቀናት ማስተኛቱ የታክሲዎችን ጉልበት፤ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ውጤታማነት እና የተባበረ እርምጃ ስኬታማነት በተግባር አሳይቷል።
አገዛዙ የአወዛጋቢውን አዋጅ ተፈፃሚነት ለሶስት ወራት ማራዘሙን ተናግሯል። ይህ ማራዘምም ከቅርብ ጊዜዓት ወዲህ ካስተዋልናቸው የማፈግፈግ እርምጃዎች አንዱ ሆኗል። የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እና የሆሳዕና የትራንስፓርት ህግ ተፈፃሚነት መዘግየት ሌሎቹ ማፈግፈጎች ናቸው።

እዚህ ላይ ሁለት ነጥቦችን ማንሳት ተገቢ ነው።
አንደኛ – ጠላት ማፈግፈግ ሲጀምር ማጥቃት መቀጠል አለበት። የአምባገነን ሥርዓቶች ውድቀት ለማፋጠን ትናንሽ ድሎችን እየሰበሰብን ለበለጡ ድሎች የሚደረገውን ትግል ማጠናከር የዘወርት ሥራችን አካል መሆን ይኖርበታል። ስለሆነም አገዛዙ የተጠየቀውን በአርኪ ሁኔታ መልሶት ቢሆን ኖሮም ሌሎች ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም ነበር።
ሁለተኛ – ለአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች ጥያቄ አገዛዙ የሰጠው ምላሽ የማፈግፈግ ምልክት ቢሆንም አርኪ ምላሽ ሊሆን ቀርቶ ግማሽ ምላሽ እንኳን አይደለም። ፓርላማ ያወጣውን አዋጅ አስፈፃሚው በየትኛው ሥልጣኑ ሊያዘገየው እንደቻለ አጠያያቂ ነው። ይህ ህገ አልባነታቸው ለምንም ነገር እንዳይታመኑ ያደርጋቸዋል። አዋጁን በአፋቸው ተራዝሟል እያሉ በተግባር ግን ተፈፃሚ እያደረጉት ስለአለመሆኑ ምንም ዓይነት ማረጋገጫ አለን? ምንም። ስለዚህም የታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች ጥያቄዎች እንኳንስ ሙሉ ግማሽም ምላሽ አላገኙም ብለን መደምደም እንችላለን። ይህ ደግሞ በተራው የሥራ ማቆም አድማው ወደፊትም ሊደገም ይችላል የሚለውን መላምት ያጠናክርልናል።
የአዲስ አበባ ታክሲ ሾፌሮችና ባለንብረቶች የሥራ ማቆም አድማ መልሶ መጀመር ስለሚቻልበት ሁኔታ መምከር እና አድማው ወደ ሌሎች የሥራ መስኮችና አካባቢዎችም እንዲዛመት መሥራት የሁላችንም ኃላፊነት ነው።
በዚህ ወቅት ህወሓትስ ምን እያሰበ ነው ብሎ መጠየቅም ብልህነት ነው።
እኔ ባለኝ መረጃ መሠረት የህወሓት ጆሮ ጠቢዎች የአድማው አደራጆችን የመለየት ሥራ ውስጥ ተጠምደው ሰንብተዋል። በተወሰነ መጠን መረጃ ያላቸው ቢሆንም የለመዱትን የጉልበት እርምጃ ለመውሰድ ድፍረት ያጡበት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል። የኦሮሚያ እና የሙስሊም ወገኖቻችን ንቅናቄ እኚህን እኩያን ጆሮ ጠቢዎች አደብ እንዲገዙ አስገድዷቸዋል። በምትኩም “ለስላሳ መንገድ” ያሉትን መፍትሄ መርጠዋል።
ለስላሳው መንገድ “ቡና እንጠጣ” ብለውታል። እንደ እቅዳቸው በየሰፈሩ ብዙ የቡና እንጠጣ ኢመደበኛ ማኅበራትን ያቋቁማሉ። እያንዳንዱ ካድሬም ጥቂት የሰፈሩን ሰው ቡና እየጋበዘ “ስለ ሰላምና ልማት” እንዲሰብክ ይደረጋል። ልዩ ትኩረት ለባለታክሲዎች፣ ሾፌሮች፣ ተማሪዎችና መምህራን እንዲሰጥ ተወስኗል። “ቡና” የተባለውም እንደ ሁኔታው ወደ ቢራና አልኮል እንዲያድግም በጀት እንዲመደብ ጠይቀዋል።
“ቡና እንጠጣ” ከቀድሞው 1 ለ 5 በመጠኑ ይለያል። 1 ለ 5 ጥርነፋ ሲሆን “ቡና እንጠጣ” ፍርሀት የወለደው ማባበያ ነው። የአሁኑ “ቡና እንጠጣ” በምርጫ 97 ዋዜዋ የነበረው የአርከበ እቁባይ ተለማማጭነትን ያስታውሰኛል። አርከበ በምርጫው በፊት የነበረው “ደግነት” ሁሉ ከምርጫው በኋላ ወደ አውሬነት መቀየሩ አይዘነጋም።
ህወሓቶች የዛሬው “ቡና ማጠጣት” ከተሳካላቸው ነገ ወደ “መርዝ ማጠጣት” እንደሚቀይሩት በበኩሌ እርግጠኛ ነኝ። ስለሆነም “ለቡና እንጠጣ” የምንሰጠው ምላሽ “እንቢ” መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ።

No comments:

Post a Comment