Friday, March 11, 2016

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዛሬም ተቃውሞዎች ቀጥለዋል

መጋቢት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ገዢው ፓርቲ የተለያዩ የመብት ጥያቄዎችን ባነሱ ዜጎች ላይ በአንድ በኩል የሃይል እርምጃውን አጠናክሮ በመቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ የአገር ሽማግሌዎችንና በህብረተሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ይኖራቸው ይሆናል ብሎ የሚያምናቸውን ሰዎች በመጥራት፣ “ልጆቻችሁን ተቆጡልን፣ ጥያቄያቸውን እንመልሳለን” በማለት መረጋጋት ለመፍጠር ቢሞክርም፣ ሳምንቱን እንደታየው ሁሉ ዛሬም፣ ተቃውሞው በተለያዩ አካባቢዎች ተካሂዷል።

ለአመታት የዘለቀው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ተቃውሞ ከጁምዐ ጸሎት በሁዋላ በአዲስ አበባ ኑር መስጂድ የተካሄደ ሲሆን፣ ምእመናኑ ከሃይማኖት ባለፈ ሌሎች የመብት ጥያቄዎችን ያዘሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።
“ብሄራዊ ጭቆናው ይብቃ፣ የተቀበረች ፍትህ ቀባሪዋን ትቀብራለች፣ ነጻነት እንፈልጋለን፣ ትግሉ እስከ ድል ደጃፎች ይቀጥላል፣ ኢፍትሃዊ ብይን አንቀበልም፣ ድምጻችን ይሰማ፣ ኮሚቴው ይፈታ” የሚሉ መፈክሮችን ጽፈው አሰምተዋል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎች እንዳይፈጠሩ አስፈላጊውን ክትትል ሲያደርጉ ቢሰነብቱም፣ ድምጻችን ይሰማ የሚታወቅበትን ሚስጢራዊ አደረጃጃት ዛሬም ተግባራዊ በማድረግ ተቃውሞው እንዲቀጥል አድርጓል።
ከተቃውሞው በሁዋላ የጸጥታ ሃይሎች አንዳንድ ወጣቶችን ይዘው ማሰራቸውንና መደብደባቸውን ለማወቅ ተችሎአል።ምን ያክል ሰዎች እንደታሰሩ ግን ለማወቅ አልተቻለም።
በኦሮምያም እንዲሁ ተቃውሞው የቀጠለ ሲሆን፣ በድሬዳዋ የላጋሬ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም በነቀምቴ ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል።
ባለፈው ማክሰኞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በአሜሪካ ኢምባሲ ፊት ለፊት ያደረጉትን ተቃውሞ የታሰሩ ተማሪዎች አሁንም አለመፈታታቸው ታውቋል። ተማሪዎቹ በጉለሌ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የሚገኙ ሲሆን፣ ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ለማየትም እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
መንግስት በኦሮምያ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በውጭ ሃይሎች የሚካሄድ ነው በማለት መግለጫ ሲሰጥ ቢቆይም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የስራ አጥነትና የመልካም አስተዳደር እጦት የፈጠሩት ችግር ነው ለማለት ተገዷል። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በጸጥታ ሃይሎች ለተፈጸመው ግድያ ይቅርታ ጠይቀዋል። መንግስት ጥፋቱን ማመኑ አንድ ነገር ቢሆንም፣ጥፋቱን ያጠፉት የጸጥታ ሃይሎችና የመንግስት ባለስልጣናት ህግ ፊት ስለሚቀርቡበት ፣ ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች ካሳ ስለሚከፍሉበት፣ ከግጭቱ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ስለሚፈቱበትና ሌሎችም የመብት ጥያቄዎች ስለሚፈቱበት ዙሪያ ምንም ፍንጭ አልሰጡም።በማህበራዊ ሚዲያ ሃሳባቸውን የሚገለጹ ኢትዮጵያውያን፣የመንግስትን የይቅርታ ሃሳብ በአብዛኛው ውድቅ ያደረጉት ሲሆን፣ ተጨባጭ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እየጠየቁ ነው።
በሌላ በኩል የመንግስትን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያወግዙ የተቃውሞ ሰልፎች በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች ተካሂዷል።

No comments:

Post a Comment