ኢሳት (ሰኔ 1 ፥ 2009)
የባህርዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች ያለ ፍላጎታቸው ከትግራይ ውልዋሎ ክለብ ጋር ግጥሚያ እንዲያደርጉ በግዳጅ ወደ አዲግራት መወሰዳቸው ተገለጸ።
የባህርዳር ከነማ ክለብ ከመቀሌው አቻው ጋር ሲጫወት ከዚህ ቀደም በደጋፊዎች በደል ቢደርስበትም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፍርደግምድል ውሳኔ ተወስኖብኛል በሚል ሲቃወም ቆይቷል።
ይህንኑ ውሳኔ የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ አጥብቀው በመቃወም ይግባኝ ቢጠይቁም ውሳኔው በመጽናቱ በአካባቢው ውጥረት እንዲነግስ ምክንያት ሆኖ ነበር።
ግንቦት 29/ 2009 ከመቀሌው ከነማ እግር ኳስ ክለብ ጋር ከዚህ ቀደም የተቋረጠው ቀሪ ጨዋታ በሁለቱ ቡድኖች መካከል እንዲካሄድ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውሳኔ ቢሰጥበትም፣ የባህርዳር ከነማ ክለብና ደጋፊዎቹ ፈቃደኛ እንዳልሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
በዚሁ ሁኔታ ግራ የተጋቡት የትግራይና የአማራ ክልል የፖለቲካ አመራሮች የመቀሌው ጨዋታ እንዲዘገይ በማድረግ የባህርዳር ከነማ ክለብ ከመደበኛው መርሃግብር ውጭ ከትግራይ ዎልዋሎ ክለብ ጋር በአዲግራት እንዲጫወት ረቡዕ ምሽት በሚኒባስ በግዳጅ ወስደዋቸዋል ተብሏል።
የባህርዳር ከነማ ክለብ እግር ኳስ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎችና ህዝቡ ወደ አዲግራት መሄዳቸውን እንዳያዩ በምሽት በሚኒባስ መወሰዳቸው ተገልጿል።
የዚህ ጨዋታ አላማም ከመቀሌ ከነማ ጋር ያለውን ውጥረት ለማርገብ የባህር ዳር ከነማ አዲግራት ሲገባ ደማቅ አቀባበል ህዝቡ እንዲያደርግለትና ይህንኑም በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ለማሳየት ሽርጉድ እየተባለ መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment