ኢሳት (የካቲት 22 ፥ 2008)
ኢትዮጵያውያን በህብረት ወራሪውን የጣሊያንን ጦር የደመሰሱበት የአድዋ ድል በዓል ወርሃ መጋቢት (ማርች) ተሰይሞለት የአድዋ ድል ወር ተብሎ ታሪኩ እየተወሳ እንዲከበር የአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ምንትጎመሪ ካውንቲ በአዋጅ ወሰነ።
መታሰቢያው የካቲት 23 ወይም ማርች 1, 120ኛው የአድዋ ድል እንዲከበር በመጥቀስ አጼ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ የመሩት ጦር በወራሪው ጣሊያን ላይ የተቀዳጀው ድል ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት ነጻ ያወጣት ሃገር ከማድረግ ባለፈ በዓሉ በየአመቱ ቢከበር የአፍሪካውያንን አንድነት የሚያሳይ ነው በማለት አዋጁ ይዘረዝራል።
እነዚሁን ነጥቦችና ኢትዮጵያን ከግምት በማስገባት መጋቢት (ማርች) ወር የአድዋ ድል እንዲሆን መወሰኑ ተገልጿል።
ዋና ጸሃፊው አይዛያው ሊጌት የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ለአካባቢው ያላቸው ጉልህ አስተዋጽዖ እውቅና በመስጠት ሁሉም ሰው ታሪካዊውን የአድዋ ድል እንዲያወድስ ጠይቀዋል።
የአድዋ ድል ታሪክ እንዲታወቅና እንዲከበር ከፍተኛ ስራ የሰራው የኢትዮጵያውያኑ ውርስና ቅርስ ማህበር በውሳኔው መደሰቱን በመግለጽ፣ በየአመቱ እንደሚያደርገው በዓሉን በዛሬው ዕለትና ነገ እሁን እንደሚያከብር አስታውቋል።
የማህበሩ ዋና ጸሃፊ አቶ የሺጥላ አርአያ በሞንትጎመሪ ካውንቲ ውሳኔ የተሰማቸውን ደስታ ለኢሳት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያውያኑ ውርስና ቅርስ ማህበር ፕሬዚንደንት የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን ረታ በበኩላቸው ውሳኔው ለኢትዮጵያውያን ያለውን ትልቅ ዋጋ በመግለጽ በሞንትጎመሪ ውሳኔ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment