ኢሳት (የካቲት 30 ፥2008)
ላለፉት በርካታ አመታት ከኢትዮጵያ ህጻናትን በማደጎ ስትወስድ የቆየችው ዴንማርክ ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ ወሰነች።
በቅርቡ ወደኢትዮጵያ በመጓዝ በማደጎ ማቆያ ጣቢያዎች ላይ ጉብኝትን ያደረጉ የሃገሪቱ ባለስልጣናት አሰራሩ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት መሆኑን በመረዳታቸው ውሳኔውን እንዳስተላለፉ ዘ-ሎካል የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
የሃገሪቱ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎም በርካታ ህጻናትን ከኢትዮጵያ ለመውሰድ ሲጠባበቁ የነበሩ የዴንማርክ ዜጎች ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ እንደተነገራቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደረጉ የዴንማርክ የማህበረሰብ ይግባኝ ቦርድ አባላት በሃገሪቱ ህጻናትን በማደጎ ለመስጠት የሚደረገው ሂደት በበቂ ስርዓት ያልተደገፈና የህጻናቱ መረጃም ያልተሟላ እንደሆነ ማረጋገጡ ይፋ አድሩጓል።
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያና በናይጀሪያ ህጻናት በህገወጥ መንገድ በማደጎ ይሸጣሉ የሚል መረጃ መገኘትን ተከትሎ ዴንማርክ ከሁለቱ ሃገራት በምትወስዳቸው የማደጎ ህጻናት ላይ ጊዜያዊ እገዳ ጥላ መቆየቷ ይታወሳል።
ይህንኑ ሁኔታ ለመከታተል ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙ የሃገሪቱ ባለስልጣናትም በስራው ላይ ክፍተት መመልከታቸውን ለሃገሪቱ ባለስልጣናት ባቀረቡት ሪፖርት አስፍረዋል።
የኖርዌይና የስዊድን መንገስትም በኢትዮጵያ ያለው የማደጎ አሰራር ግልጽነት የጎደለው ነው በሚል ፕሮግራሙን ማቋረጣቸው የሚታወስ ሲሆነ፣ ውሳኔው በሌሎች ሃገራት ዘንድም ጥርጣሬን ማሳደሩ ታውቋል።
የዴንማርክ የማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ካረን ኤሌማን ኢትዮጵያ የማደጎ አሰራርን በአግባቡ ባለመከተሏ ምክንያት ቅሬታ እንዳደረባቸውና ውሳኔው እንደተላለፈ ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ተሰማርተው ያለው የማደጎ ተቋማትም ለህጻናት ችግር መፍትሄን ከማፈላለግ ይልቅ ገንዘብ በማሰባሰብ ልጆችን በማደጎ መልክ በመስጠት ስራ ላይ በብዛት ተሰማርተው እንደሚገኙም በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉ የዴንማርክ ተወካዮች ማረጋገጣቸውን ዘ-ሎካል የተሰኘ ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
No comments:
Post a Comment