ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)
የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ከሃገር እንዳይወጡ መደረጋቸው ታወቀ።
ትናንት ከሃገር ለመውጣት ወደ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሄደው ፓስፖርታቸውን መሳሪያው ማንበብ አልቻለም የሚል ምክንያት ተሰጥቷቸው ወደቤታቸው እንደተመለሱ የተናገሩት ዶ/ር መረራ ዛሬም ኢሚግሬሽን ድረስ ሄደው የሚያናግራቸው ባለስልጣን ስብሰባ ገብቷል ተብለው ለሁለተኛ ቀን ከሃገር ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ እንዳልተሳካ ገልጸዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በቪዥን ኢትዮጵያ በተዘጋጀው ጉባዔ ላይ ይገኛሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነበር። በጉባዔው ላይ ፕሮፌሰር ጆርጅ አይቴ፣ ዶ/ር አኑራዳህ ሚተል፣ ፕሮፌሰር ጆን ሃርበሰን፣ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም፣ ፕሮፌሰር ህዝቅዔል ገቢሳ፣ አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ዶ/ር በያን አሶባ፣ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ፣ ፕሮፌሰር ሰይድ ሃሰን፣ ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው እና ሌሎች ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን የሚያቀርቡበት ሲሆን፣ ዶ/ር መረራ ጉዲናም ከሃገር ቤት ተጋብዘው እንደነበር ለኢሳት የተላከው መረጃ ያመለክታል።
No comments:
Post a Comment