መጋቢት ፳፩( ሃያ አንድ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሰሞኑን በጠረፋማ ከተሞች በተደረገው ቃለመጠይቅ ከፍተኛ የወረዳ አመራሮች ለዘጋቢያችን በሰጧት አስተያየት ከላይ ጀምሮ ያለው የክትትል አግባብ መላላቱን ተናግረዋል፡፡
“ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ ያለው የድጋፍ ስርዓት አሁን አለ ብሎ መውሰድ አይቻልም ፡፡” የሚሉት አመራር “ሃገሪቱ በበርካታ ችግሮች መወጠሯ ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር ትኩረት እንዲነፈገው አድረጓል፡፡” በማለት ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ይከሳሉ፡፡
በህጋዊ መንገድ በጠረፍ ከተሞች የሚጓዙ ስደተኞች እንኳን በአሁኑ ሰዓት ያለውን የጠረፍ እንቅስቃሴ አደገኛነት በመግለጽ ለተወሰነ ጊዜ ሁኔታዎች አስኪስተካከሉ ድረስ እንዲታገሱ ቢጠየቁ ለመመለስ ፈቃደኞች አለመሆናቸውን የወረዳው አመራር ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
“መሰራት ያለበት ስራ እሰካሁንም አልተሰራም፡፡” የሚሉት ኃላፊው በተቻለ መጠን ችግሩን ለመቀነስ በወረዳው አቅም የሚሰሩ ስራዎች ቢኖሩም ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥ አለ ለማለት እንደማያስደፍር ተናግረዋል፡፡
“በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ አሳሳቢነት በማወቅ ከላይ እሰከታች ያሉት አመራሮች ስራቸውን በአግባቡ እየሰሩ ነው ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡”በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ደላሎችን በህግ ከመጠየቅ አኳያ በርካታ ጉዳዮች ፍትህ የሚገኙበትን አሰራር በመመሪያ መሻሩ በአሰራራቸው ላይ ችግር እንደፈጠረባቸው ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የፖሊስ መኮንን ተናግረዋል፡፡
“የጠቅላይ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዮችን በጠረፍ ከተማ ወረዳዎች ቅድመ ምርመራ በማድረግ ደላሎችንና ተዘዋዋሪዎች በሚያዙበት ጊዜ በወቅቱ አስፈላጊ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችለው አሰራር በመጓደሉ መዝገቦች ቁጭ ይላሉ፡፡” የሚሉት የፖሊስ መኮንን፣ እነዚህን ጉዳዮች በክልል ደረጃ ለማከናዎን የተሸከርካሪና ፋይናንስ እጥረት መኖሩን በማሳወቅ ጥያቄዎች ቢቀርቡም ከፌደራል እስከ ዞን ድረስ መፍትሄ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ ችግሮች በየጊዜው እየተፈጠሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
“በርካታ ህገወጥ ዝውውርን የሚመለከቱ ጉዳዮችን‘ እናንተ ማየትና ማጣራት አትችሉም! ’በመባላቸው ፈጣን ምላሽ በማጣት ሲሟሽሹ ይታያሉ፡፡” በማለት የሚናገሩት የፖሊስ ባልደረባ “ደላሎች በጠረፍ ከተሞች ታስረው በቆዩ ቁጥር ያላቸውን ገንዘብ ተጠቅመው ምስክሮችን በመደለልና ከአካባቢ ስዎች ጋር በመመሳጠር በማስፈራራት የምርመራ መዝገቦች ውጤት እንደያጡ ያደርጋሉ፡፡ የገንዘብ አቅማቸውን ተጠቅመውም መዝገቡ” ወደ በላይ ፍርድቤቶች ተልኮ በነጻ እንዲሰናበት ይደረጋሉ፡፡” በማለት በአሰራሩ ላይ የሚታየውን ቸግር ይናገራሉ፡፡
“ቀዳሚ ምርመራ በአካባቢው የፍትህ አካላት አለመካሄዱ፤ መረጃዎች ሳይበረዙ በትኩሱ ተሰባስበው የህገወጥ ደላሎችንና ተባባሪ አመራሮችን አከራካሪ ለመስበር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ገትቶታል፡፡” የሚሉት መኮንን፣ የክልልም ሆነ የፌደራል መንግስት አመራሮች ለጉዳዩ ትኩረት መንፈጋቸውን መኮንኑ በቁጭት ይናገራሉ፡፡ በጠረፍ ከተሞች የሚካሄደውን ስደተኞችን የመታደግ ስራም ፍሬአልባ እንዳደረገባቸው ተናግረዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚታየው ሁሉን አቅፍ ችግሮች ህገ ወጥ ስደተኝነትን እያባባሰው ነው።
በሌላ በኩል ስድስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ታንዛኒያ ውስጥ ተይዘዋል በሕገወጥ መንገድ ድንበር ጥሰው ወደ ታንዛኒያ ገብተዋል ያላቸውን ስድስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ጨምሮ ሁለት አደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪ ታንዛኒያዊያን እንስቶችን ከተደበቁበት መያዙን የታንዛኒያ የድንበር ፓሊስ አስታውቁዋል።
የሞርጎሮ ግዛት የፓሊስ አዛዥ የሆኑት ኡሊሪች ኦኖሶፊ ”ሳንጋሳንጋ በሚባል አካባቢ ከሞርጎሮ ኢሪንጋ አውራጎዳና አቅራቢያ ላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞቹ መያዛቸውን ተናግረዋል። በወቅቱ ማንነታቸውን የሚገልጽ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ፓስፓርት አለመያዛቸውንና ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ላይ እንደነበሩም አዛዡ አስረድተዋል።”
ስድስቱ ወጣት ኢትዮጵያዊን ስደተኞች በስም ተለይተው የታወቁ ሲሆን የሃያ ዓመቶቹ ወጣት መንግስቱ ማቻሞና መሃመድ ከድር፣ የሃያ አንድ ዓመቶቹ ዘሪሁን ኦርጂናል፣ፋሪዮስ ኢንፓሙ፣ አሸናፊ ኢዮብና ብቸኛዋ እንስት የ18 ዓመቷ ወጣት ሳዲያ መሃመዲን መሆናቸውን ፓሊስ ገልጻል።
ስደተኞቹ የአውራጎዳናውን በርሃማ መንገድ ተከትለው ሲጓዙ ፓሊስ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ሊያዙ መቻላቸውንና እነሱን በማሰስ ላይ የነበሩት ፓሊሶች አደንዛዥ አዘዋዋሪ የነበሩ የ70 ዓመትና የ45 ዓመት ታንዛኒያዊያን እንስቶችን አብሮ መያዙንም አስታውቋል።
ስድስቱ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እንደሚታይ አይ ፒፒ ሚዲያ ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment