Thursday, March 3, 2016

ኦህዴድ 3 ከፍተኛ ባለስልጣናቱን ያለማእከላዊ ኮሚቴው እውቅና አሰናበተ


የካቲት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኦህዴድ አቶ ዳባ ደበሌ ፣ አቶ ሰለሞን ኩቹንና አቶ ለሲሳ ሀዩን ለማእከላዊ ኮምቴው አቅርቦ ሳያስጸድቅ መሆኑ ተረጋግጧል።
በኦሮሚያ ከተከሰተው ህዝባዊ አመጽ ጋር ተያይዞ ለዘብተኛ አቁዋም አሳይተዋል በሚል ከተገመገሙት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አቶ ዳባ ደበሌ የኦህዴድ/ኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ አባልና የኦህዴድ የጽ/ቤት ሀላፊ፣ አቶ ሰለሞን ኩቹ የጸጥታና አስተዳደር ዘርፍ ሀላፊ እንዲሁም አቶ ለሲሳ ሀዩ የከተሞችና የፖለቲካ ጉዳይ ሀላፊ ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል። የሰዎቹ መነሳት በማእከላዊ ኮምቴው ሳይጸድቅ ወሬው ቀድሞ እንዲራገብ የተደረገው የፕሮፖጋዳ ድል ለማግኘት መሆኑን የፖርቲው ምንጮች ገልጸዋል።
የኦህዴድ ማእከላዊ ኮምቴ አባላት ስራ አስፈጻሚው የሰራውን ከመገናኛ ብዙሃን መስማታቸው የኦህዴድ/ ኢህአዴግ ስርአት አልበኝነት ማሳያ ነው ሲሉ ይኮንኑታል።
ይህን ግብታዊ እርምጃ የሚቃወሙ ወገኖች መኖራቸው የኦህዴድን ከፍተኛ አመራር ለሁለት ሊሰነጥቀው ይችላል የሚል ስጋት አሳድሮአል።
የአቶ ዳባ ባለቤት ወ/ሮ ወርቅነሽ ብሩ ከወራት በፊት የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው መሾማቸው የሚታወስ ነው።
ኢሳት ከ20 ቀናት በፊት፣ የካቲት 13 ቀን 2008 ዓም ” በህወሃትና በኦህዴድ መካከል ያለው ልዩነት እያሰፋው መሄዱን፣ የህወሃት ከፍተኛ ካድሬዎች እና የኦህዴድ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት በተካሄደው ስብሰባ ላይ የሁለቱ ድርጅት ካደሬዎች በግልጽ መዘለላፋቸውን ዘግቦ ነበር። በዚሁ ዘገባ ላይ የኦሮምያ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሰሎሞን ኩቹ፣ ለግምገማ የሄዱትን የህወሃት ካድሬዎች፣ በቅድሚያ ራሳችሁን ገምግሙ፣ በክልላችን ያለእኛ ፈቃድ ጦር ማስገባት አትችሉም በማለት መናገራቸውን፣የህወሃት ልኡካን እኛን ሳታማክሩ ለምን ማስተር ፕላኑን ሰረዛችሁ ብለው ሲጠይቁም “ህወሃት በክልሉ ለሚፈጽመው ድርጊት ሁሉ፣ ኦህዴድን መቼ አማክሮ ያውቃልና” የሚል መልስ መስጠታቸው፣ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋው መሄዱንም ገልጾ ነበር።

No comments:

Post a Comment