ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2008)
ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ለነባር ታጋዮቹ ጥሪ ማድረጉ ተገለጸ። ታጋዮቹ ካለፈው መጋቢት 10 ጀምሮ በተጀመረው የህወሃት ማዕከላዊ ኮሜቴ አባላት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ መጠራታቸውም ታውቋል።
የቀድሞ የህወሃት መስራችና አመራር አባል የነበሩት አቶ አሰግደ ገብረስላሰ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለጹት፣ በጭንቀት ውስጥ የሚገኙት የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎች በውስጣቸው ቀውስና መከፋፈል ሲፈጠር ሜዳ ላይ የጣሏቸውን ነባር ታጋዮችን ለስብሰባ መጥራታቸውን ገልጸዋል። ስብሰባው በመላ ትግራይና በአዲስ አበባም እንደሚደረግ አቶ አሰግደ ለኢሳት ተናግረዋል።
በኦሮሚያ የተከሰተውን ህዝባዊ ንቅናቄ ተከትሎ የህወሃት መሪዎች ኦሮሞዎች መጡባችሁ በማለት ማስፈራራት መጀመራቸውን አቶ አሰግደ ገብረስላሴ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ ላይ ገልጸዋል። ሆኖም አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ አድማሱ ያሰፋና በአገሪቱ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ተቃውሞ በተለያየ መልክ መከሰቱን የተናገሩት አቶ አሰግደ፣ የኦሮሚያው ፈንድቶ በመውጣቱ እንጂ በሁሉም የአገሪቱ አቅጣጫዎች ህዝብ አሁን ያለውን የህወሃት አስተዳደር እየተቃወመ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተለይም በጎንደር፣ በወሎ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ህዝብ መነሳቱን የተናገሩት አቶ አሰግደ፣ ያልተነሳም ካለ አድፍጧል በማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ አፈናው ተጠናክሯል ፥ በትግራይና በጎንደር ህዝብ ላይ መጠነሰፊ አፈናና ወከባ እየተካሄደ ነው ያሉት አቶ አሰግደ፣ የትግራይና የጎንደር ገበሬ የኦሮሞ ህዝብ እያደረገ ያለውን ህዝባዊ ንቅናቄ ሙሉ በሙሉ ይደግፈዋል ሲሉም አክለው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ የመንግስት ጪሰኛ እንደሆነና የመሬት ባለቤት እንዳልሆነ የገለጹት አቶ አሰግደ፣ የኦሮሚያ ህዝብ ጥያቄ የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ መሆኑንም በመጥቀስ “ኦሮሞዎችን መጡባችሁ” የሚለው ማስፈራሪያ ማንም አልተቀበለውም በማለት ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment