የካቲት ፴ (ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ከ300 ሺ በላይ የሚሆኑ የኮንሶ ማህበረሰብ አባላት የአስተዳደር ጥያቄ መጠየቃቸውን ተከትሎ፣ በአካባቢው የሚታየው ውጥረት እንደቀጠለ ባለበት በዚህ ሰዓት ፣ የማህበረሰቡ ባህላዊ መሪ የሆኑት አቶ ካላ ገዛሃኝ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አርባምንጭ ከተማ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ከኮሚቴ አባላት መካከል አንዱ ገልጸዋል። ሌሎች የአገር ሽማግሌዎች ደግሞ የሚደርስባቸውን ወከባ በመፍራት ራሳቸውን መደበቃቸው ታውቋል። አቶ ካላ ገዛሃኝ የታሰሩት ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 26 ቀን 2008 ዓም ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ለማየት ለመጋቢት 12 ቀን ቀጠሮ ሰጥቷል።
በቁጥር 12 የሚሆኑት የአገር ሽማግሌዎች የተመረጡት መስከረም 29፣ 2008 ዓም ተደርጎ በነበረውና ከ50 ሺ ህዝብ በላይ በተሳተፈበት የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጉዳያቸውን ለክልሉ ምክር ቤትና ለጠ/ሚኒስትሩ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።በወቅቱ ችግራቸው መልስ እንደሚያገኝ ተነግሮአቸው የነበረ ቢሆንም፣ መንግስት በተቃራኒው የአካባቢውን ወጣቶች በማሰር ጥያቄው እንዲዳፈን ለማድረግ ሞክሯል። ይሁን እንጅ ህዝቡ ተቃውሞውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ ከቆየ በሁዋላ፣ ባለፈው ቅዳሜ ወደ ጅንካ የሚወስደውን መንገድ በመዝጋትና የገጠሩ ህዝብም የጦር መሳሪያ ይዞ በመውጣት ከፖሊሶች ጋር ተፋጥጦ ሳምንቱን አሳልፏል።
የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ወደ ገጠር በመግባት በዶክቱ፣ ዱራይተ፣ ካሆ፣ ዳራ፣ ኮልመና እና ጃርሶ ቀበሌዎች በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፣ በርካቶችንም ይዘው አስረዋል። ባለፉት የቅርብ ሳምንታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኮንሶ ተወላጆች በኮንሶ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ውስጥ ታስረዋል። ከታሰሩት መካከል የወረዳውን አስተዳዳሪ ጨምሮ 5 የወረዳው ምክር ቤት አባላት ይገኙበታል። ባለስልጣኖቹ የታሰሩት የህዝብ ጥያቄ ደግፋችሁ ቆማችሁዋላ በሚል ምክንያት ነው።
ከሽማግሌዎች አንዱ ለኢሳት እንደተናገሩት በአካባቢው ትምህርት ቤቶችና የመንግስት መሰሪያቤቶች አሁንም እንደተዘጉ ናቸው። በርካታ ሰራተኞችም ከመንግስት የሚደርሰውን ጥቃት ለመሸሽ አካባቢውን ለቀው ሄደዋል።
ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ከዚህ በፊት የኮንሶ ህዝብ ተወካዮችን አነጋግረው ጉዳዩን አጣርተው በአጭር ጊዜ መልስ ለመስጠት ቃል
ቢገቡም በተቃራኒው በክልሉ ልዩ ሀይል የአፈና ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠሉ ጥያቄያቸውን መመለስ እንደደተሳናቸው አስገንዝቦናል በማለት ሽማግሌዎቹ መናገራቸው ይታወሳል።
ለደቡብ ክልል ብሄር ብሄረሰቦች ም/ቤት ቅርበት ያላቸው አንድ ባለሙያ በሰጡት አስተያየት የኮንሶ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢነት ያለውና የኮንሶ ተወላጅ በሆኑ አንዳንድ የኢህአዴግ ሹማምንት ጭምር ድጋፍ ያለው ቢሆንም፣ ይህን ጥያቄ መመለስ በክልሉ ለሚገኙ ከ55 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች ተመሳሳይ ጥያቄ እንዲያነሱ መንገድ መክፈት በመሆኑ ምክንያት ክልሉ ጥያቄውን ከኮንሶ ሕዝብ ጋር መክሮና አሳምኖ ሃሳባቸውን ማስቀየር፣ይህ ካልተቻለ ደግሞ በሃይል ከመጨፍለቅ የተሻለ አማራጭ የለውም ብለዋል፡፡በተለይ ጠ/ሚኒስትሩ በሊቀመንበርነት የሚመሩት ፓርቲ እንዲህ ዓይነት አነስተኛ የሕዝብ ጥያቄ እንኩዋን ሰላማዊ በሆነና በሰለጠነ መንገድ መመለስ አለመቻሉ ትልቅ የሕዝባዊ ውግንና እና የአመራር ብቃት ላይ ጥያቄን የሚያስነሳ ነው ሲሉ መናገራቸውን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ሰገን አካባቢ ዞን በአሁኑ ወቅት ኮንሶን ጨምሮ 8 ብሄር ብሄረሰቦች የሚገኙ ሰሆን ከእነዚህ መካከል ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የያዘው የኮንሶ ህዝብ ነው፡፡
No comments:
Post a Comment