ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2008)
ከኢትዮጵያ ወደጎረቤት ኬንያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር መጨመረን ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት በችግሩ ዙሪያ ምክክርን በማካሄድ ላይ መሆናቸውን የኬንያ መገኛኛ ብዙሃን ዘገቡ።
በኬንያ የድንበር አካባቢ በምትገኘው ማንዴራ ግዛት የሚገኙ የኢሚግሬሽን ሃላፊዎች ከዶሎ ከተወከሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር በኬንያ ምክክር እያደረጉ መሆኑን ዘስታር የተሰኘ ጋዜጣ ባቀረበው ሪፖርት አመልክቷል።
ባለፈው ወር ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ኬንያ የተሰደዱ ሲሆን፣ የሃገሪቱ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናትም ድርጊቱ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
የስደተኛ ኢትዮጵያውያኑ ቁጥር መጨመር ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት ባለስልጣናት የስደተኞቹ ቁጥር በሚቀንስበትና የድንበር ቁጥጥርን ለማጠናከር ይረዳ ዘንድ የጋራ መድረክ ማዘጋጀታቸው ታውቋል።
የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በየዕለቱ በትንሹ 30 ኢትዮጵያውያን ወደኬንያ በመሰደድ ላይ መሆናቸውን የሚገልጽ ሲሆን አብዛኞቹ ስደተኞቹም ወጣት ወንዶች መሆናቸው ታውቋል።
የኬንያ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት የሃገራቸው መንግስት አዲስ በጀትን በማጽደቅ የድንበር ቁጥጥሩ እንዲጠናከር እርምጃን እንዲወስድ በማሳሰብ ላይ መሆናቸውንም ዘስታር ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።
ቁጥራቸው በትክልል ሊታወቅ ያልቻለ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የኬንያ እስር ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ ሃገሪቱ በርካታ ስደተኞችን ያለፍላጎታቸው ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ እቅድ መያዟም ተገልጿል።
ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ከለላን የሚፈልጉ ስደተኞች ተላልፈው ሊሰጡ ይችላል በሚል በኬንያ መንግስት ላይ ቅሬታን እያቀረቡ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል።
No comments:
Post a Comment