ኢሳት (የካቲት 23 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት አጋጥሞት ያለው የውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተባባሰ ባለበት ወቅት ባለፉት ስድስት ወራት ከውጭ ንግድ የተገኘው ገቢ ማሽቆልቆሉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ረቡዕ አስታወቀ።
ሃገሪቱ ከውጭ ንግድ የምታገኘው ገቢ እየቀነሰ መምጣቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ላይ ተፅዕኖ ከማሳደሩ በተጨማሪ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ጫናን እንደሚፈጥር የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስድስት ወራቶች ከውጭ ንግድ ገቢ ከሶስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢን ለማግኘት አቅዶ የነበረ ቢሆንም 2.4 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መቻሉን ባንኩ አመልክቷል።
የተገኘው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑን የገለፀው ባንኩ ሃገሪቱ ባለፈው በጀት አመት ከውጭ ንግድ 5.8 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷን አውስቷል።
በተያዘ የ2008 በጀት አመት ካለፈው አመት የተሻለን ገቢ ለማግኘት እቅድ ተነድፎ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ስድስት ወራት ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገቡ ተገልጿል።
የወጪ ንግድ ገቢ ማሽቆልቆልም በውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ላይ ተፅዕኖን እንደሚያሳድርና የዋጋ ግሽበቱን ሊያባብስ እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።
በቅርቡ በሃገሪቱ የተፈጠረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ባንኮች የሚያደርጉትን የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ለመቆጣጠር አዲስ መመሪያን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።
ይሁንና፣ የውጭ ምንዛሪን ለማግኘት ወረፋን እየተጠባበቁ የሚገኙ የንግድ ኩባንያዎች በበኩላቸው የቁጥጥሩ ተግባራዊ መደረግ ችግሩን አባብሶት እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የአለም ባንክ እና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ሃገሪቱ ያጋጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለባት ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የውጭ ሃገር ባንኮች በሃገሪቱ ቅርንጫፎች ከፍተው በባንክ ስራ ላይ እንዲሰማሩ ፈቃድ መስጠቱም የሚታወቅ ነው።
No comments:
Post a Comment