Friday, March 18, 2016

በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች ወደ ረሃብ ሊደርስ በሚችል ደረጃ መመደባቸው ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 9 ፥ 2008)

በአፋርና በሶማሊ ክልሎች እንዲሁም በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ በርካታ ዞኖች ወደረሃብ ደረጃ ሊሻገር በሚችል ድረጃ ውስጥ መመደባቸውን የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ትንበያ የሚሰጥ ፋሚን ኧርሊ ዋንርኒንግ (Famine Early Warning System) የተባለ ድርጅት አርብ ይፋ አደረገ።

በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን የድርቅ መባባስ ተከትሎ አብዛኛው የሰሜን አርቶብ-አደር አካባቢዎች ደረጃ አራት ተብሎ በሚመደበውና ለረሃብ አንድ ደረጃ በቀረው ሰንጠረዥ ውስጥ መመደባቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
ምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ፣ ዋግ ህምራ፣ እንዲሁም ሰሜን ወሎ አካባቢዎች በዚሁ አስጊ በተባለው ደረጃ አራት ውስጥ የተፈረጁ ሲሆን የድርቁ አደጋ ወደ አስከፊ ሁኔታ እየተቀየረ መምጣቱ ተገልጿል።
በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋን መባባስ ተከትሎ ሃሙስ የመንግስት ባለስልጣናት ከአለም አቀፍ ማህበረሰብ አዲስ ጥሪ ማቀረባቸው ይታወሳል።
በደረጃ አራት ውስጥ የተፈረጁት አካባቢዎች በቅርቡ አስቸኳይ እርዳታ የማይደርስላቸው ከሆነም ችግሩ ወደ ረሃብ ደረጃ በሚመደበው ደረጃ አምስት ውስጥ ሊሸጋገሩ እንደሚችልም ስጋት መሆኑን ይኸው አለም አቀፍ ተቋም ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
አብዛኛው የትግራይ እና አምሃራ አካባቢዎች እንዲሁም የማዕከላዊና ምስራቅ ኦሮሚያ ደረጃ ሶስት ወይም የድርቅ ቀውስ ውስጥ መመደባቸውን በአሜሪካው አለም አቀፍ የልማት እርዳታ (USAID) ስር የሚሰራው ይኸው ድርጅት ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስትና አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ተረጂዎች የ1.4 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ጥያቄን ቢያቀርቡም እስካሁን ድረስ ከግማሽ በታች ብቻ የሚሆነው መገኘቱ ታውቋል።
የአለም አቀፍ ድጋፍ መዘግየትም በተረጂዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን በማሳደር ድርቁ ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋትን አሳድሮ እንደሚገኝ የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።
በሃገሪቱ አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰ ይኸው የድርቅ አደጋ በቀጣዮቹ ሁለትና ሶስት ሳምንታት ውስጥ ምላሽን ካላገኘው ወደስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ተረጂዎች የሚቀርብላቸው እርዳታ እንደማይኖር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በድጋሚ አስታውቋል።
አልጀዚራ ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሮይተርስ፣ ኤቢሲ ኒውስ፣ አሶሼትድ ፕሬስ፣ ቢቢሲ እና ሌሎች አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን በዚሁ የድርቅ መባባስ ዙሪያ አርብ የተለያዩ ዘገባዎች ማቅረባቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

No comments:

Post a Comment