ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)
ነዋሪነታቸው በዚህ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሱርማ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰውን የግፍ እርምጃ በመቃወም እንዲሁም በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ያለን ግድያንና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመቃወም በአሜርካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ።
የተለያዩ መፈክሮችን በማስተጋባትና በማንገብ ማክሰኞ ረፋድ ሰላማዊ ሰልፉን ያካሄዱት ኢትዮጵያውያን የአሜሪካን መንግስት ለሰብአዊ መብት መከበር ቁርጠኛ አቋሙን እንዲያሳይ ጠይቀዋል።
በቅርቡ በደቡብ ክልል ኦሞ አካባቢ በጸጥታ ሃይሎች በሱርማ ብሄረሰብ ተወላጆች የተፈጸመን ኢሰብዓዊ ድርጊት ያወገዙ ሰልፈኞች በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በወልቃይትና፣ በጋምቤላ ክልል እንዲሁም በመላ ሃገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የጋራ ግብረ ሃይል እንዲሁም ከተለያዩ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና የሲቢክ ማህበራት በጋራ በተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የዋሽንግተን ዲሲ ከተማና አካባቢዋ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ ተሳታፊ መሆኑም ታውቋል።
በመላ ሃገሪቱ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመባባስ ላይ መሆናቸውን ምክንያት በማድረግ የማክሰኞች ሰላማዊ ሰልፍ መዘጋጀቱንና በተሳካ መልኩ መከናወኑን የሰልፉ አዘጋጆች ለኢሳት ገልጸዋል።
በዚሁ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት አዘጋጆቹ በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ ነው ያሏቸውን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማቅረባቸው ታውቋል።
ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ላለው ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ሃላፊነትን እንደሚወስድ ተናግረዋል።
የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ምስል በማንገብ ተቃውሞኣቸውን ሲያቀርቡ ያረፈዱት ኢትዮጵያውያኑ የአለም አቀፍ ማህበረሰብም በሃገሪቱ እየተፈጸሙ ባሉ ኢሰብዓዊ ጥሰቶች በቂ ትኩረትን እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ከሶስት ወር በፊት በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ይህንኑ ተቃውሞ ተከትሎ ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት መንግስት ተቃውሞን ለመቆጣጠር የሃይል እርምጃን ሲወስድ መቆየቱን ይገልጻሉ።
አሜሪካና የአውሮፓ ህብረትም ድርጊቱን በመኮንነን መንግስት ለተነሳት ጥያቄ ሰላማዊ ምላሽን እንዲሰጥ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment