መጋቢት ፮ (ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ በኦህዴድ ውስጥ የተነሳው የውስጥ እንቅስቃሴ አለመቋጨቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ ከተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ የድርጅቱ አባላት ለሁለተኛ ዙር ግምገማ ዛሬ ወደ አደማ እንዲገቡ ተደርጓል።
የተለያዩ መስሪያ ቤት የቢሮ ሃላፊዎች፣ የየዞን ባለስልጣናት፣ የካቢኔ አባላትና ሌሎችም ባለስልጣናት ለከፍተኛ ግምገማ መጠራታቸውን ምንጮች ገልጸው፣ ግምገማው ለ10 ቀናት የሚቆይ ሲሆን፣ ከግምገማው በሁዋላ ተቃውሞ ተጠናክሮ በቀጠለባቸው ቦታዎች የሚገኙ ባለስልጣናት ሊባረሩ ይችላሉ።
በቅርቡ በተደረገው ግምገማ 4 ከፍተኛ የኦህዴድ ባለስልጣናት ከስልጣናቸው እንዲባረሩ ተደርጎ ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ማታ በአደማ የዩኒቨርስቲ ግቢ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ተከትሎ ከፍተኛ ንብረት ወድሟል። ተማሪዎች ሌሊቱን ውጭ ያሳለፉ ሲሆን፣ ዛሬም ግቢውን ለቀው ወጥተዋል።ቃጠሎውን ማን እንዳደረሰው አይታወቅም። የፌደራል ፖሊሶችም ግቢውን መውረራቸው ታውቋል። በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ተመሳሳይ ቃጠሎች መድረሳቸው፣የቃጠለው መንስኤ በክልሉ ከሚካሄደው ተቃውሞ ጋር ሳይያያዝ እንደማይቀር ይገመታል።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች መጠነኛ ተቃውሞች ሲካሄዱ የዋሉ ሲሆን፣ የመከላከያ ሰራዊት አባላት አሁንም በክልሉ ያላቸውን ይዞታ እያጠናከሩ ነው።
ሂውማን ራይትስ ወች በበኩሉ በኢትዮጵያ የኦሮምያ ክልል ለደረሰው የሰብአዊ መበት ጥሰት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል እንዲያጣራው ጠይቋል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ እንዳለው በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስብአዎ ቀውስ እየተፈጠረ ነው። ምንም እንኳ ችግሩ በአለማቀፍ ደረጃ መጠነኛ የሆነ ትኩረት ቢስብም፣ ከምርጫ 97 ወዲህ በኦሮምያ የሚታየው ፖለቲካ ቀውስ ትልቁ ነው ብሎአል። ወታደሮችና የጸጥታ ሃይሎች በርካታ ዜጎችን መግደላቸውን እንዲሁም በርካታ ሰዎች ባልታወቁ ቦታዎች መታሰራቸውን ገልጸዋል። ምንም እንኳ በአንዳንድ አካባቢዎች መጠነኛ የሆኑ ግጭቶች የነበሩ ቢሆንም እንዲሁም የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ቦታዎች ተቃውሞ ሰላማዊ ነበር ብሎአል።
ከ4 አመታት ወዲህ መንግስት ሆን ብሎ የነጻውን ሚዲያ በማፈኑና የሲቪክ ሶሳይቲ ተቋማትን በማዳከሙ መረጃዎችን ለማግኘት እና የደረሰውን ጉዳት በትክልል ለማጣራት ባያስችልም፣ የመንግስት ሃይል የተቀላቀለበት እርምጃ አገሪቱን ወደ አደገኛ ጎዳና እየመራት ነው፤በዘላቂ መረጋጋቷና እድገቷ ላይም ተጽእኖ ማሰራፉ አይቀርም ሲል ድርጅቱ አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ካውንስል የኢትዮጵያ መንግስት ሃይል የተቀላቀለበት እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ እንዲሁም የታሰሩት እንዲፈቱ ጥሪ እንዲያቀርብ፣ የጠየቀው ሂውማን ራይትስ ወች፣ በሚደረገው ማንኛውም ምርመራ ላይ ተአማኒነትን፣ ገለልተኛነትንና ተቀባይነትን እንዲያገኝ ለማድረግ አለማቀፍ ማህበረሰቡ ሊሳተፍበት ያስፈልጋል ሲል ምክሩን ለግሷል።
No comments:
Post a Comment